The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ለምን አልወጣም?

የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ወቅታዊ ይዞታ

ጴጥሮስ አሸናፊ

በከፍተኛ ጉጉት እየተጠበቀ ያለው የድምፃዊ፣ ዜማና ግጥም ደራሲ ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞ ኢትዮጵያ የተሰኘው አዲስ አልበም ይለቀቃል ተብሎ አስቀድሞ በተያዘለት ቀን ማለትም ለዳግሚያ ትንሳኤ ለስርጭት እንደማይበቃ ለማረጋገጥ ተችሏል።

ከአርቲስቱ፣ ከአታሚውና አከፋፋይ ወገኖች በጋራ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ለህትመት የሚሆኑ ግብአቶች አቅርቦት እጥረት፣ የህትመት መሳሪያዎች የማምረት አቅም(efficiency) በተፈለገው መጠን አለመሄድ፣ የአከፋፋዮችና የህዝብ ፍላጎት(demand) መጨመርና ሌሎችም ቴክኒካዊና ያልታሰቡ ክስተቶች (unforseen circumstances) ለስርጭቱ መዘግየት ምክንያቶች መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል።
የአዲሱ ኢትዮጵያ አልበም ህትመት ሙሉ በሙሉ በሃገር ውስጥ ባሉ ድርጅቶችና የህትመት መሳሪያዎች እንደሚሆን ከዚህ ቀደም ማሳወቃችን የሚታወስ ነው። ይህም ማለት ቅጂው ወይም ድምፅ የሚያርገፍበት ኮምፓክት ዲስክና የዲስኩ ማቀፊያ ቤት ወይም ከቨርን ጨምሮ በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ ይሆናሉ ማለት ነው።
አስቀድሞ አልበሙን ለማተምና ለዳግሚያ ትንሳኤ ለስርጭት ለማብቃት ሲታሰብ፤ የማሽኖቹን የማምረት አቅምና ለመጀመሪያ ዙር (ቅድመ ዳግሚያ ትንሳኤ) ከ350 ሺህ እስከ 400 ሺህ እትም ለሙዚቃ አፍቃሪው ለማድረስ የሚቻልበትንም በማስላት ነበር።
ቴዲ አፍሮ በገበያ በሚቀርበው እያንዳንዱ ዲስክ የ14 ዘፈኖቹ ሙሉ ግጥሞች፣ የሙዚቃ አቀናባሪዎቹ ፎቶዎች፣ ከአልበሙ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ምስሎች፣ የምስጋና መልእክትና ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲያካትት በመፈለጉና ይሄንንም አከፋፋይና አታሚ ወገኖችም በተስማሙት መሰረት የማባዛት ስራው የተጀመረ ቢሆንም፤ አልፎ አልፎ በሚያጋጥሙ ግብአቶች እጥረት የተፈለገውን ያህል ቅጂ በታሰበው ጊዜ ለማድረስ አልተቻለም።
የህትመት ስራውን የወሰደው አካል የህትመት ማሺን በቀን በሙሉ አቅሙ 30 ሺህ ኮፒ ያህል ማባዛት የሚችል ቢሆንም ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ማሽኖችን ከሌሎች ማተሚያ ቤቶች መከራየት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ተግባራዊ ተደርጓል። ከዚህ ጎን ለጎንም በአልበሙ ዙሪያ የማርኬቲንግ ቅድመ ትንበያና ጥናት ሲያካሂዱ የሰነበተው ቡድን የሙዚቃ አፍቃሪውን የመግዛት ፍላጎት፣ በተለይም ለትንሳኤ ዋዜማ የተለቀቀው “ኢትዮጵያ” ነጠላ ዜማ በአጭር ቀናት ውስት የሚያስመዘግበውን የተመልካችና አድማጭ ብዛትና ሪከርድ፣ በሃገር ውስጥ ከሁሉም ክልሎች አልበሙን ለማሰራጨት ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ቁጥር በየጊዜው መጨመር፣ በተቆራጠ ጊዜ ወደ ህትመት ሲገባ በሚኖሩት ክፍተቶች ሊፈጠሩ የሚችሉ የኮፒ ራይት ጥሰቶችንና ህገወጥ ቅጂዎችን ለመግታትና ሌሎችም ተጨማሪ ጥናቶች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከዚህ ቀደም ለመጀመሪያው ዙር ቅድመ ዳግሚያ ትንሳኤ ከ350 ሺህ እስከ 400ሺህ ኮፒዎች ለማተምና ለማከፋፈል ታቅዶ የነበረውን ወደ 600 ሺህ ማሳደጉ አስፈላጊ መሆኑ በ3 ቱም ወገኖች ስለታመነበት ለተግባራዊነቱም ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሚሆነውን ይሄን አሃዝ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን የህትመት ሂደቶች ታሳቢ በማድረግ ለስርጭት የሚደርስበት ቀን ከሚያዚያ 24 ቀን 2009 ዓ/ም በፊት ሙሉ በሙሉ ለሙዚቃ አፍቃሪው ማድረስ እንደማይቻል ስለታመነበት፤ ሌሎች ያልታሰቡ ክስተቶች ካልተፈጠሩ በስተቀር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ማክሰኞ ሚያዚያ 24 ቀን 2009 ዓ/ም ወይም ሜይ 2 ቀን 2017 ዓ/ ም ለህዝብ ይደርሳል።
ከሃገር ውስጥ ስርጭት ጎን ለጎን ከሃገር ውጭ በአራቱም መአዘን አልበሙን ለማከፋፈል ፍላጎት ያላቸው የንግድ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦችን በተመለከተ በቴዲ አፍሮ ኦፊሴላዊ ድረ ገፅ http://www.teddyafromuzika.com ላይ የተቀመጠውን ፎርም በመሙላት ወይም በስልክ ቁጥሮች +12062098597 ወይም +41762250266 በመደወል ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል ከዚህ በፊት የተገለፀ ሲሆን፤ አሁንም አከፋፋይ ባልተገኘባቸው ሃገሮች ወይም ከተሞች ለማከፋፈል ፍላጎት ያላችሁ ከዚህ በላይ በተቀመጡት የመገናኛ ዘዴዎች መረጃ ማግኘት የሚቻል ይሆናል።
ኢትዮጵያ የተሰኘው አዲሱ የቴዲ አፍሮ ነጠላ ዜማ ለህዝብ ከደረሰ አንድ ሳምንት የሆነው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ነክ በሆኑ መገናኛ ብዙሃንና ማኀበራዊ መድረኮች መነጋገሪያ በመሆን ግምባር ቀደም ሲሆን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ በአጭር ጊዜ በርካታ ተመልካች በማግኘትም የራሱን ሪከርድ በየጊዜው እየሰባበረ ይገኛል። ዜማው በተለቀቀ በ8ኛ ቀኑ በቴዲ አፍሮ ኦፊሴላዊ የዩ ትዩብ ቻናል ብቻ ከ1ሚሊዮን 700 መቶ ሺህ በላይ ተመልካች አግኝቷል። ይሄም ማለት በቀን በአማካይ ከ212 ሺህ 500 ገዜ በላይ ታይቷል ማለት ነው። ይሄን የዩትዩብ ቪዲዮ በአድናቂዎቹ ወደ ፌስ ቡክ ብቻ ከ 23 ሺህ ጊዜ በላይ ተጋርቷል። አሁንም ይህ ቁጥር በሌሎች ትዩቦች፣ ድረ ገፆች፣ በፌስቡክና ትዊተር የሚለቀቁትን አያካትትም። ከነጠላ ዜማው መለቀቅ በኋላም የቴዲ አፍሮ ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፅ ጎብኚ ቁጥር እያደገ የመጣ ሲሆን በአንድ ሳምንት ብቻ ከ26 ሺህ በላይ ተከታዮችን በማፍራት በአጠቃላይ ቁጥሩን ከ 1 ሚሊዮን 709 ሺህ በላይ አድርሶታል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲሱ አልበም ከተካቱት 14 ዘፈኖች አንዱ የሆነው “ጎጃም ማሬ” የተሰኘ ዜማ ተሰርቆ ካለ አርቲስቱና ሕጋዊ አከፋፋዮቹ ፈቃድ በማኀበራዊ መድረኮች በከፍተኛ ሁኔታ ሲሰራጭ እየተመለከትነው ነው። በርካቶች ዕውን ይሄ ዜማ የተሰረቀ ነው ወይ? በአዲሱ አልበም ውስጥስ ተካቷል ወይ? ከማን እጅ ሊሰረቅ ቻለ? ወዘተ የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱም እያየን ነው። ስለዚህ ዜማ ማለት የሚቻለው በአዲሱ አልበም ከሚካተቱት 14 ዘፈኖች አንዱና በአማኑኤል ይልማ የተቀነባበረ በተለይም በታላቁ ደራሲ አዲስ ዓለማየሁ ድንቅና ተወዳጁ የፍቅር እስከ መቃብር ድርሰት መሰረት ያደረገ ታሪካዊ ስራ መሆኑን ነው። አሁን በየማኀበራዊ ሚዲያው የምንሰማው ከመጨረሻ ቅጅ ወይም (ማስተር) የተወሰደ ባለመሆኑ ከፍተኛ የጥራት ችግር ይሰማበታል። በዚህ አጋጣሚ ይሄን ሕገ ወጥና ሊወገዝ የሚገባው የስርቆት ተግባርን ላለማበረታታትና ለአርቲስቱም ክብርና ፍቅር ሲባል ዜማውን ላለማሰራጨት ለተባበራችሁ የመገናኛ ብዙሃንና የማኀበራዊ መረብ ተጠቃሚዎች በግሌ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ይሄ ዜማ ከቴዲ አፍሮ እጅ እንዴት ወጣ? ማንስ ለማኀበራዊ መረቦች አሰራጨው? ለምን? የሚሉትን ደግሞ ጊዜው ሲፈቅድ እመለስበታለሁ።
መልካም የዳግሚ ትንሳኤ በዐል
ጴጥሮስ አሸናፊ

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a comment