The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

መልስ – ይህን ነበር የምንፈራው! – ብስራት ደረሰ – ከአዲስ አበባ (አንዱዓለም ተፈራ)

አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

እሁድ ሚያዝያ ፳ ፪ ቀን ፳ ፻ ፱ ዓመተ ምህረት

ይህ፤ ከላይ በሰፈረው ርዕስ፤ በሳተናው ድረገጽ ላይ ለተቀመጠውና ላነበብኩት ጽሑፍ መልስ ነው።

 

ባደባባይ ወግና ስርዓት ያልተላበሰ፤ ሃሳቡን ቶት ጸሐፊውን ወይንም ከጀርባው አለ ተብሎ የሚጠረጠርን ጉዳይ ፍለጋ የመሄድ አባዜ በሰፈረብን ባሁኑ ወቅት፤ ዐማራነታችን አይፈቅድልኝምና፤ ወጣ ብዬ፤ እርስዎ በጭንቀትዎ ምክንያትና በቅንነት የሠጡንን ምክር ተመርኩዤ፤ ግድ የለም አይጨነቁ የሚል መልስ አለኝ።

ይድረስ ለአቶ ብስራት ደረስ ብዬ ብጽፍ፤ ደስ ባለኝ ነበር። ነገር ግን፤ እንደርስዎ የተጨነቁ ብዙዎች ስላሉ፤ ይሄን የምጽፈው ብዛት ላለው እንደርስዎ ለተጨነቀው ክፍል ጭምር ስለሆነ፤ ይድረስ ለስዎን ትቼ፤ ለርስዎ መልስ በማለት የተጨነቁበትን ጉዳይ አብራራዋለሁ። ጭንቀትዎትን መረዳቱ ለኔ አልከበደኝም። እዚያ ቦታ እኔም ነበርኩበት እላለሁና! ነገር ግን አሁን እግሬን ሰደድ በማድረግ፤ ሌሎች ቀድመውኝ ከደረሱበት ዐማራነት እኔም ስለደረስኩ፤ ምናልባት ልግባባዎት እችላለሁ ብየ ነው። እንዳሉት፤

“አንድ አዲስ ነገር በቀላሉ አይለመድምና እኔን የመሰሉ ብዙ “አማሮች”/አማሮች በተወሰነ ደረጃ እንቅፋት ሊሆኑባችሁ ይችላሉ። ዝም ብለው ማለቅን መርጠው ሳይሆን ሁሉም ነገር ተወነባብዶባቸው ነውና በነሱም ብዙም አትፍረዱባቸው። ይሄ የመሆንና ያለመሆን ሼክስፒራዊ ጥያቄ ትልቅ ራስ ምታት ነው።”

መቼም ይሄ ብዙ ቁም ነገሮችን ያዘለ ነው። የርስዎን ጭንቀትና እኔ በመልስነት ላቀርበው የፈለግሁትን ገለጻም የያዘ ነው። እርስዎ እንዳሉት በኢትዮጵያዊነት ተወልደን፤ በኢትዮጵያዊነት አድገን፤ ጥርስ አብቅለን ቀንድ ማብቀሉ የቀረን ሰዎች፤ “የሸመገለን ውሻ፤ አዲስ መሸወጃ መንገድ ማስተማር አትችልም!” እንደሚሉት ፈረንጆቹና፤ እርስዎም ጥሩ አድርገው እንዳስቀመጡት፤ “ዐማራነታችሁ የት ገባ?” ተብለን ስንጠየቅ፤ “ምኑን አመጣህብኝ ደግሞ! ዞር በል ከፊቴ!” ማለታችን፤ የአስተዳደጋችን ውጤት ነው። መቼም ዕውቀት የሚገኘው ከገጠመኞቻችን ነው። ያላየነውን፣ ያልሰማነውን፣ ያላሸተትነውን፣ የልዳሰስነውን እና ያልቀመስነውን ልናውቅ አንችልም። እርስዎ እንዳሉት ይህ አዲስ ሆኖብናል።

መቼም ብዙ ከርስዎ ጋር የምስማማናቸው ጉዳዮች አሉኝ። እነዚያን አንስቼ ድንቅነታቸውን ብዘርዝር፤ አንባቢን ማስልቸት ይሆንብኛል። የእርስዎን ጽሑፍም እንዳያነቡ መሻማት ይሆንብኛል። ስለዚህ ጎላ ብለው የወጡ እስርዎ ያነሷቸውና ያሳሰቡኝ ጉዳዮች ስላሉ፤ በነሱ ላይ ላተኩር እወዳለሁ።

የመጀመሪያው፤ ”ሕወሓት ፖሊሲውን ማስተካከል አለበት።” ብለው ያሰፈሩት ነው። በርግጥ ለርስዎ ጠፍቶዎታል ብዬ አይደለም። ይህ ድርጅት እኮ ሲፈጠር፤ “በዐማራው መቃብር ላይ የትግራይን ሩፑብሊክ እመሠርታለሁ!” ብሎ ነው። ይህ እኮ! አጥንትና ሥጋው፣ ደምና ቆዳው ነው! እንዴት አድርጎ ነው፤ ይሄን የሚቀይረው። ይሄንማ ካደረገ፤ ሕልውናው በነነ ማለት ነው። የደረደረው የውሸት ታሪክና ያደረገው ትግል ሟሾ ጠፋ ማለት ነው። “ተኩላ ቁመቱንና ለምዱን ቀይሮ በግ ይሁን!” ማለት አይሆንብንም!

ማናችንም ብንሆን ድርጅቱን በድርጅትነቱ ወይንም የትግሬዎቹ ብቻ በመሆኑ አልጠላነውም። የድርጅትነቱ መሠረት ግን፤ ዐማራውን ለማጥፋት መሆኑን ባደባባይ ያወጀው ዓላማ ነው። የዐማራው መነሳሳት እኮ በዚህ ተመርኩዞ በደረሰበት በደል የተተከለ ነው!

ወደ ሁለተኛው ጉዳይ ልግባ። “ከተባበርን ችግራችን ቀላል ነው።” ያሉት ነው። በጣም፣ በጣም ትክክል ነዎት! ያለምንም ማወላወል ከጎንዎ እቆማለሁ። ዐማራው በትብብር ይሄ የትግሬዎቹ መንግሥት ቢጠፋ፤ ይህ ሁሉ ችግር አይደርስበትም ነበር። ሀቁ ግን ሌላ ሆነ። አማራው ተለይቶ መቃብሩ ሲቆፈርለት፤ ማን አይዞህ አለው። በርግጥ ዐማራው በሙሉ ባድን ላይ ቶሎ አብሮ አልቆመም። ገና ከሥር መሠረቱ ግን የተወሰኑም ቢሆኑ፣ ዐማራዎች እምብኝ! ብለው፣ ከፋኝ! ብለው፣ ቆመው ያልተገደሉ፤ በትግል ሕይወታቸውን ያጡ አሉ። እርስዎ ከኔ የበለጠ የሚያውቋቸው ሞልተዋል። ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የዚህ ቁጥር አንዱ ናቸው። ዐማራው ዐማራነቴ ወንጀል አይደለም ያለው ዛሬ አይደለም። ኢትዮጵያዊነቴ ያድነኛል ብሎ፤ አብዛኛው ዐማራ በዚያ እየታገለ ቆየ እንጂ፤ በዐማራው ላይ የተለየ በደል የለም ብሎ ክዶ አልተቀመጠም። በኢትዮጵያዊነቱ ታግሏል። ያ በኢትዮጵያዊነቱ የከፈለው መስዋዕትነት ግን፤ ያ ለትብብር ያጠፋው ሕይወት ግን፤ በዐማራው ላይ እየደረሰ ያለውን በደል፤ ላንዲት ሰኮንድ አላረገበለትም። ትብብሩ የትም አልደረሰም።

ከሞላ ጎደል ብዙዎቹን የየድርጅቶቹ መሪዎች በግል ስለማውቃቸው፤ እንዲተባበሩ ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ ተንበርክኬ ያልለመንኳቸው የሉም። አሁንም ዐማራው አልተባበርም አላለም። መተባበሩ ግን ቸግሮታል። በዐማራው ሕይወት ላይ የሚኖር ትብብር ግን፤ ዐማራውን ወደ ጎን ትቶ ለመሄድ የሚወሰደው እርምጃ ግን፤ አደጋ አለው። እናም ዐማራው ረጋ ብሎ ቆሞ፤ የትብብሩን ጉዳይ፤ ከሕልውናው ጉዳይ አንጻር ተመልክቶታል። ሕልውና ሲኖረው ነው መተባበር የሚችለው። ስለዚህ መጀመሪያ ልኑር አለ እንጂ፤ አልተባበርም አላለም። በኔ ላይ እየተደረገ ያለውን የዘር ማጽዳት ዘመቻ የተገነዘበና፤ ኢትዮጵያን ለማዳን አብሬ አጥፊህን እዘምትበታለሁ ለሚል፤ ዐማራው እጆቹ እንደተዘረጉ ናቸው። ተጠቂነት ግን እንዲተባበር አያደርገውም።

ወደ ሶስተኛው ነጥቤ ልመለስ፤ “ዕዝ እኮ ነው። ዕዝ መጥፎ ነው። አታስቀረውምም። በጸሎትና በምህላ፤ እንዲሁም በተባበረ ክንድ፤ ልታለዝበውና ልታመክነውም ትችላለህ። እኛ የሳትነው ይህን ነው።” ያሉትን ይመለከታል። እንደኛ ሕዝብ በጾምና በጸሎት ተማምኖ የሚኖር ያለ አይመስለኝም። ይህ ግን የተጠናና መሠረት ያለው ቀረቤታ ሳይሆን፤ በፍላጎቴና በስሜቴ ተመርኩዤ ያቀረብኩት ነው። በዚህም ይሁን በዚያ፤ በኔ እምነት፤ ስህተቱ ያለው ይህን ዕዝ አለማመናችን አይደለም። ይልቁንም ይህን ዕዝ ማመናችን እና ሙጥኝ ብለን ጨምድደም መያዛችን ነው። በዕድገታችን፤ የሥጋውንም ሆነ የነፍሱን ሁሉ ነገር፤ አድራጊና ወሳኝ አምላክ ነው ብለን፤ የራሳችንን ኃላፊነት ላለመውሰድና ለማናውቀው ሁሉ ተጠያቂ አምላክን በማድረግ፤ ለራሳችን ማምለጫ መልስ እንሠጣለን። ይህ ትክክል አይደለም።

በመጀመሪያ፤ በመሬት ላይ “ጥረህ ግረህ ብላ!” የሚለውን ሽምጥጠን እንክዳለን። ቀጥሎ እያንዳንዳችን በግል የዓለም ኑሯችን ላይ፣ እንደ አንድ ግለሰብ “በሠራነው፤ በግል ተጠያቂ ነን! የአባት ኃጢያት ለልጅ አይሆንም!” የሚለውን እንደብቃለን። ሌላ ደግሞ፤ “ሁሉም ፍጡር በፈጣሪ ፊት እኩል ነው። ሁሉም የፈጣሪ ሥራ ነው። ሁሉም መሬት የፈጣሪ ነው። ሁሉንም እኩል ያያል!” የሚለውን እንዳልሰማን ጆሯችንን እንክዳለን። ልጨምርና፤ በሥጋ ያለውን ለነፍስ፣ የነፍሱን ለሥጋ ማዛመዳችን ችግር ነው። ይህ እኮ ግለሰቦች የሚያደርጉት ተግባር ነው።

እንዴት ነው በዚህ ዓለም አንዳችንን ቀጥቶ፤ ሌላችንን እንዲጠቅም ጾምና ጸሎት የምናደርገው! ከኖኅ ጥፋት በኋላ፤ ምን ተባለ! በግል ተጠያቂ የምንሆንበትን ጉዳይ፤ በአንድነት እንደ ኢትዮጵያዊ ወይንም እንደ አማራ ልንጠየቅበት አንችልም። ስለዚህ፤ እንደ አማራና እንደ ኢትዮጵያዊ ስንኖር፤ በአንድነት ነው። ስንሞትና በአምላክ ፊት ለፍርድ ስንቀርብ፤ እንደ አንድ የሱ ፍጡር፤ በግለሰብ ደረጃ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለብቻ፤ የክርስትና ተክታዮችም ሆኑ የእስልምና ተካታዮች፤ ወይንም እምነትን ያልተቀበሉ፤ በኢትዮጵያዊነታችን ገነት አንገባም። መለስ ዜናዊና እርስዎ በኢትዮጵያዊነታችሁ፤ እኩል ልዩ ቦታ አይሠጣችሁም። ኢትዮጵያዊያንን የጨረሰና ሰውን ርስ በርስ ያባላው መርዘኛው ተባይ፤ ከርስዎ ጋር ኢትዮጵያዊ ነውና ባንድ ገነት ትገባላችሁ የሚል ቅዠት የለኝም። ኢትዮጵያዊነት የሥጋ ጉዳይ ነው። ስለዚህ፤ ጾምና ጸሎት ለየግል ገነት መግቢያ እንጂ፤ ለሀገር ማዳኛ አይደለም። ሀገር ሲዖል አይገባም። ሀገር ገነት አይገባም። ኢትዮጵያን ከሌሎቹ የራሱ ሀገሮች ለይቶ ገንጥሎ፤ ወደ ሰማይ አይወስዳትም። በአንድነት ሲዖል አንገባም። ጾምና ጸሎት ለሀገራችን ችግር መፍትሔ አይደለም። የኛ ጥረት ብቻ ነው ከችግራችን ነፃ የሚያወጣን። መማሪያ አእምሮው፤ መተግበሪያ እጆቹ ከኛ ጋር ናቸው። እኒህን ተጠቅመን መፍትሔ መሥጠቱ የኛ ኃላፊነት ነው። አምላክ ዐማራን ሊያጠፋ የትግሬዎቹን ገዥዎች አልፈጠረም። መፈጠሩና ማደጉም ሆነ መቀጠሉ፤ የኛው ድክመት ነው።

ቁልጭ ባለ አጭር ሁለት አረፍተ ነገሮች መልሱን አስቀምጠውታል። “በመሠረቱ አማራ አይፈረድበትም። ራሱን ለማዳን የሚወስደው እርምጃ ሁሉ ቢያስመሰግነው እንጂ አያስወቅሰውም!” በማለት። ያለ ምንም ቁጥእባ፤ ይሄን ከርስዎ ጋር መቶ በመቶ እጋራዎታለሁ። የጠቅላላው ጥያቄ መልስም ይሄው ነው። ዐማራው ራሱን እንዲከላከል ተገዷል። እናም ይሄንኑ ነው እያደረገ ያለው። በተለይ እንደ እርስዎና እንደኔ ኢትዮጵያዊ ተብሎ ሳይሆን፤ “ዐማራ ነህ! ዐማራ ነሽ! ዐማራነት ወንጀል ነው! ታሪክህና ታሪክሽ እርጉም ነው! በኢትዮጵያ ለደረሰው ሁሉ ጥፋት ያንተና ያንቺ ወገን ነው ተጠያቂው!” እየተባሉ ያደጉ ወጣቶች ናቸው አሁን የተነሱት። ስለዚህ፤ “ይሄ እኔን ጥፋተኛ አድርጎ የወነጀለ የነሱ ኢትዮጵያዊነት፤ ለኔ መጥፊያ ሆነ እንጂ፤ ምን ጠቀመኝ!” ብለው ቢደራጁ፤ የተፈጥሮ ግዴታቸውን ፈጸሙ እንጂ፤ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተግባር አልፈጸሙም።

ሌላው ጉዳይ የዐማራውን ማንነት በተመለከተ ያሰፈሩት ነው። “የፈራሁት መድረሱ ካልቀረ አሁን የሚያሳስበው አማራው ማን ነው? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ማንም በቀላሉ ሊመልሰው የማይችል ከባድና ጠንቀኛ ጥያቄ ነው፡፡” በማለት አስቀምጠዋል። ለኔ ግን የሚያስፈራና የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ፤ የዐማራው ትግል፤ በማንነት ላይ የሚደርስን በደል መቃወም ነው። ይህ ማለት፤ ማንም “እኔ ይሄን ነኝ!” በሚልበት ጊዜ፤ አይደለህም ወይንም በዚያ ምክንያት በደል ይደርስብሃል፤ የሚለውን መቃወም ማለት ነው። ስለዚህ፤ ዐማራ ማነው? የሚለው፤ ለጥያቄ አይቀርብም። አንድ ከመቶም ሆነ ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ የአማራ ደም ያለው፤ አማራ ነኝ እስካለ ድረስ፤ አማራ ነው። የአማራ ደም ሳይኖረውም አማራ ነኝ ካለ፤ አማራ ነው። ይህ የግል ግንዛቤን እንጂ፤ የሌላውን ፍርድ የሚጠይቅ አይደለም። በርግጥ አደረጃጀትንና አመራርን አስመልክቶ፤ በአንድ ድርጅት የተካተቱ የድርጅቱ አባላት፤ የሚከተሉት የራሳቸው መንገድ ይኖራቸዋል። ይህ ለጠላት ሰርጎ ገብነት በር ላለመክፈት የሚከተሉት የራሳቸው መለኪያ ነው። ለዐማራነት ግን፤ ዐማራ ነኝ ያለ ሁሉ ዐማራ ነው። ስለዚህ ችግር የለም።

ለኔ ችግር የሚሆነው፤ “እነዚህኞቹ ቀላል ናቸው፡፡” በማለት፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን፤ ነን የሚሉትን ማንነት ያለ ጥያቄ ተቀብሎ፤ ዐማራውን ግን፤ “ዐማራ ነኝ!” ሲል፤ “ተመርመር!” ማለቱ ላይ ነው። “አማራ ነኝ የሚልንስ? አማራ እንዳልሆነ ልናውቅበት የሚያስቸለን የምርመራ ዘዴ በፍጹም ልናገኝ አንችልም” ላሉት ደግሞ፤ እኛ ልናውቅ የምንፈልገው ማነን? “ዐማራ ነኝ!” ያለውን ሰው፤ ዐማራነቱን ለማረጋገጥ የሚነሳው፤ ማን መብት ሠጠው? ይሄን ለኪ ደግሞ፤ የራሱን ማንነት የለካለትስ ማነው? ይሄን ጥያቄ መመለስ ሊኖርብን ነው። እዚህ ላይ፤ ድርጅት ሌላ፤ ማንነት ሌላ መሆኑን ለማስረገጥ እንጂ፤ እርስዎ ይሄን ይስቱታል ብዬ አይደለም።

በርግጥ፤ “የአማራ ዘር በየቦታው የተበተነ ነው፡፡ በክፍለ ሀገር ያልተወሰነ፣ በጎሣና በነገድ ያልተዋቀረ፣ አልፎ አልፎ እንደሚስተዋለው በመንደር ልጅነት ካልሆነ በስተቀር እሳት እንደተጠጋው የናይሎን ጨርቅ በአማራነት በቀላሉ የማይጨማደድና እንደ አንዳንድ ጉዶች ወደጢሻና ጉድባ ወርዶ የማይኮማታተር በተፈጥሮው ቦርቃቃ አስተሳሰብና አመለካከት ያለው ሕዝብ ነው።” በማለት፤ ባንድ በኩል ዐማራውን የምንነት ትርጉም ሲሠጡት፤ በሌላ በኩል የዐማራውን መኖሪያ ጠቁመዋል። በየቦታው ተበታትኖ መኖሩ ማንነቱን አያደበዝዘውም። እኔ አሜሪካ ተቀምጬ፤ አሁንም ዐማራ ነኝ። ያ የመኖሪያ ቦታዬ፤ የኔን ማንነትና የማንነቴን እምነት አይሠርዘውም። አዎ! እኔ አይደለሁም ካልኩ፤ ያ የራሴ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ዐማራ መሆኔ ብቻ ሳይሆን፤ ለዐማራው ሕልውና አሁንም ለመታገል ተነስቻለሁ። የአሁን መኖሪያ ቤቴ ግን አሜሪካ ነው። እናም ዐማራው፤ የትግሬዎች ገዥ ቡድን በሠጠው ቦታ ሊካለልና፤ በዚያ ብቻ መታወቂያ ወረቀት ቢሠጠው፤ ያንን አይቀበልም። ለዚህም ነው፤ ከዚህ የትግሬዎች መንግሥት ጋር፤ ኢትዮጵያ መንግሥት የላትምና፤ ዐማራው የሞትና ሽረት ትግል እያደረገ ያለው።

ስጋትዎን፤ “ግን ሁሉም ነገር የጨረባ ተዝካር ሆነና ሰሚ ጠፍቶ ይሄውና አንዱ የኢትዮጵያዊነት ያማረ ሠበዝ ራሴን በነገዴ ላደራጅ እያለን ነው።” በማለት፤ ራስዎን ተቃርነው አቅርበዋል። ዐማራው በዐማራነቱ ተደራጅቶ ራሱን ከመጥፋት ለማዳን የተነሳው፤ ይሄ የጨረባ ተዝካር ሆኖና ሰሚ ጠፍቶ አይደለም። የትግሬዎቹ ገዥ ቡድን፤ ዐማራነትህ ወንጀል ነው ብሎ ሊያጠፋው ሲነሳ፤ አልጠፋም ብሎ ራሱን ለማዳን ነው የተደራጀው። ርስዎም ቢሆን፤ ይህ ጉዳይ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ፤ ራሱን አደራጅቶ ለመከላከል መነሳቱ፤ ግድ እንደሆነበት ከላይ አስፍረዋል። በዚህ ላይ አጣጣሉትና ቅር አለኝ። ራሱን አደራጅቶ ለመከላከል የተነሳን አማራ፤ የጨረባ ተዝካር ብሎ በዚያ መስፈሩ፤ ትክክል አይደለም።

ከዚያ በተረፈ የለገሱት ምክር ጠቀሜታ አለው። ነገር ግን፤ እኒህ በዐማራነታቸው የተደረጁ፤ ይሄ ሁሉ ጠፍቷቸው አይደለም። ላለመሞት ትግሉን ማካሄድ ግድ ሆኖባቸው ነው። እናም እንዳይደገምና ተጠያዎቹ ፍርዳቸውን እንዲያገኙ፤ የግድ መደራጀት ብቻ ሳይሆን፤ ጠንካራ ሆኖ መገኘቱ፤ የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ ነው። ምክርዎ ዋጋ አለው። ዐማራዎች ወደ አንድ በመሰባሰብ፤ ፍራቻም ሆነ የተለየ ሃሳብ ያለን፤ መነጋገር እንችላለን። ተደራጅተን መታገሉ ግን ለውይይት የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። በተግባር ውሏል።

ከምክርዎት መካከል፤ “አማራ በአማራነት የመደራጀት ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሠራሽ ጠባይ ስለሌለው የኢትዮጵያ ጉዳይ ከወያኔዎች እጅ ወጥቶ መልክ እስኪይዝ ድረስ ብቻ በመለስተኛ መርሐ ግብርነት የአማራነትን የመታገያ ሥልት በጊዜያዊነት ብትይዙ የኃጢኣቱ ሥርየት ከሁለት አቡነ ዘበሰማያት ባልዘለለ የንስሃ ቀኖና የሚገኝ ይመስለኛልና እምብዛም የሚያስወቅሳችሁ አይሆንም።” ብለዋል።

ድንቅ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፤ ይህን ማድረጉ ማስወቀስ ሳይሆን ማስመስገን ይገባዋል። በተጨማሪም በዐማራነት መደራጀት ተፈጥሯዊ ግዴታ የሆነው፤ ዐማራነትን ለማጥፋት የተነሳ የትግሬዎች ገዥ ቡድን ስላለ ነው። በዚህ ጊዜ፤ ተፈጥሯዊ ግዴታ የሚሆነው፤ በዐማራነት ተደራጅቶ ራስን መከላከሉ ነው። ይሄንን አለማድረጉ ተፈጥሯዊ አይደለም። በዐማራነት የተደራጀ አካል፤ የዐማራው ሕልውና ተረጋግጦ፤ ለወደፊትም ይሄ አደጋ እንዳይከሰት መዋቅሯዊ ማስተማመኛ እስካልተፈጠረ ድረስ፤ ይኖራል። ዐማራው ራሱን ማኖር ተፈጥሯዊ ግዴታው ነው።

ሌላው ርስዎን ያሳሰበዎት ጉዳይ፤ “የአማራነት ስሜት ከራሱ ከብዙ አማራ እንኳን ሩቅ በሆነበት ሁኔታ የአማራን ብሔርም በሉት ጎሣ በአማራነት ማሰባሰቡ ከባድ ነው – ክብደቱ ደግሞ እንኳንስ ወደ ተግባሩ ገብተውበት ገና ሲያስቡት ጭንቅላት ያዞራል፡፡ አማራ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደወተት ሊመሰል ይችላል – ያልገባበት ጓዳና ጎድጓዳ ስለሌለው ተሰበጣጥሯል፤ መሰበጣጠሩም በልዩነት በማያስታውቅ ሁኔታ ነው፡።” ያሉት ነው።

አይቸገሩ ከባድ አይደለም። አሁን በመጥፋት ላይ ያለን፤ የዘር ማጽዳት እየተካሄደበት ያለን ወገን ማሰባሰቡ፤ ከሚገምቱት በላይ ቀላል ነው። ይልቁንም ቀድሞ ተሰባሰቦ፤ በከተማና በገጠር፤ በሰላማዊ መንገድና በትጥቅ አመጽ ውሎበታል። አዲስ የሚፈጠር ጉዳይ አይደለም። ከከፋኙ መሪ ከገብረመድሕን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ፤ ተደራጅተው በጠለምት፣ በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ ባርማጨኾ፣ በበየዳ፣ በላሄንና ሻግኔ፣ በድብባህር፣ በዋግ፣ በራያ፣ በጎጃምና በሸዋ ሲዋደቁ ቆይተዋል። አሁን ትናንት ሸዋ ላይ ሬሳቸውን እየጎተት፤ ሬሳን ለማጥቃት የተሰለፈን ፈሪ የትግሬዎች ስብስብ የሚያስደነግጥ ትግል፤ ዐማራ ነን ብለው እያካሄዱ ነው። እናም አዲስ አይደለም። እኛ የያዝነው ቀጣዮች ሆነን ነው።

እርስዎ እኮ አንጥረው አስቀምጠውታል። “ዛሬ የአማራው ሀብትና ንብረት በትግሬዎች ቁጥጥር ሥር ነው የሚገኘው – ነፍሱም ጭምር፡፡” በማለት።  ይሄን ምስክርነትዎን እጅ ነስቼ ተቀብየዋለሁ። ይህ ግንዛቤ ነው፤ አሁን ተደራጅተው ያሉትን የዐማራ ታጋዮች፤ ባደባባይ በመመካከር፤ ሌላም ዱር ቤቴ ያሰኛቸው። እናም እስከዛሬ ዝም ብለው አለመቀመጣቸው ለዚህ ነው። ለተቆርቋሪነትዎና ለምክርዎ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።

EMF

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: