The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ከሃይለማሪያም በስተጀርባ ያለው ” ስሁል ሚካኤል ” ማን ነው? – ቬሮኒካ መላኩ

ብዙ ጊዜ የአለፉ አገር መሪዎችን ታሪክ ማንበብ እወዳለሁኝ ። ይሄን የማደርገው የመሪዎች ባህሪ ፣ አመራር ጥበብ ፣ ጥንካሬ ፣ ድክመት የአገርንም የህዝብንም እጣ ፋንታ ሲወስን አንብቤለሁኝና ወይም አምናለሁና የመሬዎችን ታሪክ ማንበቡ ፋይዳው ብዙ ነው የሚል የግል እምነት ስላለኝ ነው።
አፄ በካፋ የተባሉት ንጉስ ጎባጣ ነበሩ አሉ ። ታዲያ በዙሪያቸው የነበሩት መኳንንቶች ፣ መሳፍንቶች ቀጥ ብለው ከሄዱ ቁመታቸው ንጉሱን ስለሚበልጥና ይሄም ንጉሱን ሊያስከፋቸው ይችላል ብለው ስለሚያስቡ ንጉሱን ለመምሰል ጎበጥ ብለው ይሄዱ ነበር አሉ ።ይሄን የተመለከተው ህዝብ ” እንደ ንጉሱ አጎንብሱ! ” ማለት ጀመረ ይባላል ። “የጎባጣ አሽከር አጎንብሶ ይሄዳል ። ለምን? ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል ነዋ ” የምትባለውም አባባል ከዚሁ የተያያዘች ሳይሆን አይቀርም ።
እኔ ሳስበው እነዚያን መኳንንቶች “የሚጎብጡት ” ንጉሱ አስገድደዋቸው ሳይሆን ይልቁንስ ለሀይለኛው የማደግደግ ሰውኛ ባህሪያው ስለሆነ ይሆናል።
ጆሴፍ ስታሊንም የግራ እጁ ከቀኝ እጁ አጭር ስለነበረች ባለስልጣናቱ አይናቸውን ወደዛች አጭር እጅ ከወረወሩ ጣጣው ከባድ እንደ ነበር ይነገራል ።
እኛም በጊዜያችን በህይወት ያለ ሳይሆን ከሞተ 3 አመታት ያለፈው መሪ አነጋገር ፣እጅ እንቅስቃሴ ፣ መነፅር አደራረግ ፣ ምንም ሳያስቀር ኮርጆ የሚተገብር መሪ እየተመለከትን ነው ። ልዩነቱ የድሮዎቹ መኳንንቶች የሚያደገድጉት ለህያዋን ሲሆን ይሄኛው ለሙት መሆኑ ነው ።

ዛሬ ስታሊንንም በካፋንም ማንሳቴ ” የእኛው ጉድ ” ስለሆነው “ጠቅላይ ሚንስትር” ልፅፍ ፈልጌ ነው ። ” ጠቅላይ ሚኒስትር ” የሚለውን ማእረግ በትምህርተ ጥቅስ ማስገባቴ እስካሁን ጠቅልሎ ስለማያውቅ ወደፊትም ይጠቀልላል ብዬ ስለማልገምት ነው።

የዚህ ፅሁፍ አላማ የታዘዘውን የሚያወራው እና ስራ የተባለውን የሚሰራውን ሃይለማሪያምን መገምገም ሳይሆን ከመጋረጃው ጀርባ ያለውን “ስሁል ሚካኤልን ” መፈለግና ማፈላለግ ይሆናል ።
በመጀመሪያ “ስሁል ሚካኤል ማን ነው? ” የሚል አንባቢ አይጠፋምና በዚህ ላይ ትንሽ ጊዜ ላጥፋና ወደ ዋናው ጉዳይ እገባለሁኝ ። ራስ ስሁል ሚካኤል በ1750 ዎቹ ከትግራይ ወደ ጎንደር በአፄ ኢዮአስ ዘመነ መንግስት ጊዜ በአንገቱ ድንጋይ አስሮ እና አደግድጎ ለደጅ ጥናት ወደ ጎንደር ቤተ መንግስት ገባ ።
ስሁል ሚካኤል ወደ ጎንደር የሄደው ትግራይ ውስጥ በደል ስለበዛበት የደረሰበትን በደል ለማመልከት ነበር ። ነገር ግን ስሁል በደሉን አመልክቶ ወደ ግዛቱ ወደ ትግራይ ከመመለስ ይልቅ እዛው ጎንደር ቤተመንግስት በመቅረት እንደ አማካሪም በመሆን እያገለገለ ቆየ ። እየዋለ እያደረ ተንኮል እየሸረበ እና እየገመደ ቤተ መንግስቱን ማተራመስ ጀመረ ። በመጀመሪያ የራስ ሚካኤል ስሁል የመጀመሪያ ሰለባ የሆነው ንጉስ ኢዮአስ ነበር ። ንጉስ ኢዮአስን በሻሽ አንቆ ከገደለ በኋላ ከአምባ ግሸን የ 70 አመቱን አዛውንትና አንድ እጁ የተቆረጠውን ዮሃንስ በማምጣት አፄ ዮሃንስ ብሎ አነገሰ ።

አምባ ግሸን ወይም ወህኒ አምባ የሚባለው ቦታ በዛ ዘመን የነጋሲ ዘር ያላቸውና በስልጣን ላይ ያለው ንጉስ ሲሞት የሚተኩት ልኡላን የሚከማቹበት ቦታ ነበር ። የአምባ ግሸን ጉዳይ (ወህኒ አምባ) ራሱን የቻለ አስደናቂ ታሪክ ስላለው ወደፊት እመለስበታለሁኝ ። ራስ ሚካኤል ስሁል ኢዮአስን በሻሽ አንቆ ከገደለ በኋላ ራሱ በኢዮአስ ዙፋን ያልተቀመጠው የነጋሲነት ዘር ስላልነበረው እና ቢነግስ ህጋዊነት እና ቅቡልነት ከህዝቡ እንደሚነፈገው በመረዳቱ ነበር ።
በዚህም አማካኝነት ያለው አማራጭ እጅግ ደካማውን ፣ እጀ ቆራጣውን እና የ70 አመቱን ዮሃንስን ዙፋኑ ላይ አስቀምጦ ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ በአሻንጉሊቱ ንጉስ አማካኝነት አገር ማስተዳደር ጀመረ ።

አሻንጉሊት ከሆንክ Use and throw (ተጠቅሞ መወርወር) ነውና አሁን የመጣል ባለተራ የ70 አመቱ አዛውንት አፄ ዮሃንስ ሆነ ። ትኬቱን ስሁል ቆረጠ ። ስሁል ሚካኤል ይሄን ንጉስ ለ 1 አመት ከተጠቀመበት በኋላ እንደፈለገው አልታዘዝለት ሲል በ1761 ከምግብ ጋር መርዝ አብልቶ ገደለው ። የ70 አመቱን አዛውንት በመርዝ ከገደለ በኋላ ከአምባ ግሼን የሟቹን ዮሃንስን ልጅ ተክለሃይማኖትን አስመጥቶ አነገሰ ። በዙፋኑ ላይ አፄ ተክለሃይማኖት ለስሙ አንግሶ ከመገረጃ ጀርባ ሲገዛ ለትንሽ አመታት ከቆየ በኋላ ህዝቡ ስለአመፀበት ሸሽቶ ወደ ትግራይ ሄዶ እዛው አገሩ ሞተ ።

አሁን በመጠኑም ቢሆን የራስ ስሁል ሚካኤልን ታሪክ ያስረዳሁ መሰለኝ ። ስለዚህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ” ራስ ስሁል ሚካኤል ” የሚለው ስም የሚወክለው አሻንጉሊት ንጉስ አስቀምጦ ከመጋረጃ ጀርባ ያለ ፣ ዋና ስልጣን ያለው ፣አድራጊ ፈጣሪ ሰው ማለት ነው ። ፈረንጆቹ ” King Maker ” የሚሉት መሆኑ ነው ።

የታሪክ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ” ታሪክ ራሱን ይደግማል ። አይደግምም ። ” እያሉ ጎራ ለይተው ይከራከራሉ ።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበረው ሄንሪ ኪሲንገር “ ታሪክ ራሱን ይደጋግማል ። ማንኛውም በምድር ላይ የተነሣ መንግስት በተመሳሳይ መልኩ በመጨረሻ ከመፈራረስ አልዳነም” ብሏል ። በመቀጠልም “ታሪክ ከሽፈው የቀሩ ጥረቶች፣ ሳይፈጸሙ የቀሩ ምኞቶች ጥርቅም ነው። . . . ስለዚህ የታሪክ ተመራማሪ የሆነ ሰው አሳዛኝ ሁኔታ መምጣቱ የማይቀር መሆኑን ተቀብሎ ለመኖር ይገደዳል” ብሏል ።

ኮሚኒስት ፈላስፎች በተቃራኒው “ታሪክ ራሱን አይደግምም ባይሆን በአዲስ መልክ ይከሰታል ” ይላሉ። ዲዲሮ እንደሚለው ፈላስፋ ይሄን በምሳሌ ሲገልፅ << በአንድ ጅረት ውስጥ ሁለት ጊዜ አትታጠብም ። የታጠብክበት ውሃ አልፎ ወርዷል ። እንደገና የምትታጠበው በአዲስ ውሃ ነው ። >> ይላል ።

እኔ በበኩሌ ከ250 አመታት በፊት ስሁል ሚካኤል ያነገሰው እጄ ቆራጣው እና የ 70 አመቱ አሻንጉሊት አዛውንት ከ 250 አመታት በኋላ መለስ ዜናዊ ከጎለተው የ 58 አመቱ ” ጠቅላይ ሚንስቴር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ስለሚመሳሰልብኝ ታሪክ ራሱን ይደግማል የሚሉትን ምሁራን እቀበላለሁኝ ። ዋናውን ጉዳይ ትቼ የታሪክ ትንታኔ አበዛሁ መሰለኝ ባይጠቅማችሁም አይጎዳችሁም በማለት ነው።

አንባቢ እንድረዳልኝ የምፈልገው ይሄ ፅሁፍ ስለአገራችን ኢትዮጵያ የፖከቲካ ሁኔታ ቢዳስስም ፅሁፌ የሚያተኩረው ህውሃት እና ሃይለ ማሪያም ደሳለኝ ላይ ብቻ ነው ። በእኔ እምነት ሌሎቹ ድርጅቶች በራሳቸው ሂይወት የሌላቸው ግኡዝ የሆኑ እንግዴ ልጆች ናቸው የሚል እምነት ስለአለኝ ነው ።

ህውሃት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በለስ ቀንቶት አራት ኪሎ ቤተመንግስት ከገባ ጀምሮ አገሪቱን የገዛበትን የአገዛዝ ዘዴ በሶስት ዋና ዋና ወቅቶች መክፈል እንችላለን ።

1) ከ 1983 _ 1993 ~ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የህውሃት የስልጣን ዘመን በድርጅቱ ውስጥ ጎልቶ የወጣ እና ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ስልጣን ያለው ሰው አንድም አልነበረም ። በነዚህ 10 አመታት መለስ ዜናዊ በሽግግሩ ጊዜ የፕሬዚደንትነት እና ከሽግግሩ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ቢኖረውም የፈላጭ ቆራጭነት ስልጣን አልነበረውም ። በዚህ 10 አመታት ህውሃት ይከተል የነበረው የአመራር ዘዴ ከበርሃ ይዞት የመጣውን Collective Leadership ( በህብረት መምራት) ባህል ነበር ። በዚህም መሰረት እነዚያ 10 አመታት ህውሃት እንደ ድርጅት በጋራ በመወሰን ሲገዛ ኖሯል ።

2) ከ1993 _ እስከ መለስ ዜናዊ ሞት ድረስ ~ የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ በተከሰተው የህውሃት ክፍፍል የመለስ ዜናዊ ቡድን ማሸነፉን ተከትሎ አገሪቱ ህውሃት ከሚባል የሽፍታ ቡድን መመራት ወደ አንድ አምባገነን መሪ የተሸጋገረችበት ወቅት ነበር ። በእነዚህ አመታት ህውሃት ማለት መለስ ዜናዊ ማለት ነበር ። በ 1993 አም መለስ ዜናዊ ክፍፍሉን አሸንፎ ከወጣ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ብቅ አለ። በእነዚህ አመታት ህውሃት ብቻ ሳይሆኑ ብአዴን ፣ ኦህዴድ ፣ ዴኢህዴን እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ይተነፍሱ የነበሩ በመለስ ዜናዊ ሳምባ ነበር ።

3) ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ _ ዘመነ አሻንጉሊት ።
እነዚህ አጭር አመታት የአገሪቱ ፖለቲካ መዋህር በማን ላይ እንደሚሽከረከር ያልታወቀበት ፣ አገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ በፖለቲካ ተቃውሞ እየተናጠችበት ያለበት ወቅት ነው ። የፖለቲካ ንጠቱ ( Political turmoil) ምን እንደሚወልድ አወዛጋቢ የሆነበት አመታት ናቸው ። አሁን የምንገኝበት ወቅት ለፖለቲካ ተንታኞች ፈታኝ የሆነበት ወቅት ይመስለኛል ።

ለመሆኑ ከሃይለማሪያም ጀርባ ሆኖ አሻንጉሊቱን የሚያዘው ማነው ??
አባይ ፀሃዬ ነው? ስብሃት ነጋ ነው? ሳሚራ የኑስ ነው ? ጌታቸው አሰፋ ነው? ደብረ ፂዮን ነው? ማነው? ማነው ማነው? ሃይለማሪያም ደሳለኝ የተባለ ግራማፎን ካሴት አጉርሶ የሚያስወራው ማነው?

መቼም ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ፈጣሪ ለጉድ የፈጠረው ነው ። በኢትዮጵያ የታሪክ መፃህፍት የዚህን ሰው የአሻንጉሊትነት ታሪክ የተጋራ አምሳያ አላነበብኩም ። ቅድም ከላይ የጠቀስኩት ስሁል ሚካኤል ያስቀመጠው እጄ ቆራጣው የ 70 አመቱ አዛውንት አፄ ዮሃንስ እንኳን አንድ አመት ብቻ አሻንጉሊት ሆኖ በስሁል ሚካኤል መዘወሩ ስለአስመረረው “እምቢኝ ” ብሎ ሞቱን መርጧል ።

ሃይለማሪያም ደሳለኝን ካለፉ የኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ማነፃፀር ከባድ እንደሆነ ይገባኛል ። እሱም ራሱ “መሪ ነኝ ” ብሎ ደፍሮ ለህሊናው የሚናገር አይመስለኝም ያውቀዋላ ። ከሌሎቹ መሪ ከነበሩት ማወዳደር ቢከብደንም እስኪ ከልጅ ኢያሱ ጋር እናነፃፅረው ።
ልጅ ኢያሱ ስልጣን ሲይዝ 13 አመት ታዳጊ ልጅ ነበር። ሃይለማሪያም ስልጣን “በየሰዘበት ” ወቅት የ 55 አመት ሰው ነበር ።
ልጅ ኢያሱ በ 13 አመት እድሜው “ሞግዚት አልፈልግም ” ብሎ አገር ማስተዳደር ጀመረ ። ብዙ ለውጥ አመጣ ። ኋላ ቀር የነበረውን እና ለዘመናት ረግቶ የነበረውን “ሌባሻይ ” እና “ቁራኛ ” የተባለውን የፍትህ ስርአት አስወግዶ በዘመናዊ ፍትህ ስርአት ተካው። በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የፖሊስ ሰራዊት አቋቋመ ፣ ዘመናዊ ኦዲት ሲስተም ተከለ ፣ በሃይማኖትም በኩል ትልቅ ለውጥ አመጣ ። ከሁሉም የበለጠ በሰማይ በምድሩ የተከበሩ የነበሩትን እነ ራስ አባተ ቦያለውን በማሰር ስልጣን እንዳለው ለህዝቡ አረጋገጠ ። ልብ በሉ ይሄ የ 13 አመት ልጅ ነበር ።
አሁን ስለሃይለማሪያም ምን ላውራ ? ባስብ ባስብ ምንም አላገኘሁም ። ደከመኝ ።

ሰሞኑን እንደምንሰማው ህውሃት ቢያንስ ለሁለት ቢበዛ ለሶስት ተከፍሏል ይባላል ። ይህ በሆነበት ሁኔታ የሃይለማሪያም ደሳለኝን “ስሁል ሚካኤል ” ማወቅ ብዙ ጥቅም አለው። ከአመት በፊት በኢህአዴግ ውስጥ በተደረገ ግምገማ ሃይለማሪያም ብልጭ ብሎበት ስብሃት ነጋን ” ስጋ እንዳየ ጩልሌ ዙሪያየን ሲዞረኝ ይውላል ” ብሎ ተናግሮ ነበር ። ሃይለማሪያምን የሚያዘፍነው ድጄ ስብሃት ነጋ ይሆን እንዴ? ።

በህውሃት ሰዎች ዘንድ ለአመታት ብሃት ነጋ “King Maker ” እንደሆነ ይወራል ። ሰውየው ኦፊሻል የሆነ የፖለቲካ ስልጣን ባይኖረውም እንደፈለገ ሲዘላብድ ይውላል ።
ነጋሶ ጊዳዳም በፃፈው መፅሀፍ ” ፕሬዚደንት በነበርኩበት ወቅት አቦይ ስብሃት እሁድ እሁድ ቤተመንግስት እየመጣ ዋና እንዋኝ ይለኝና በምንዋኝበት ወቅት ትእዛዝ የሚመስል ነገር ጣል አድርጎብኝ ይሄዳል ” ብሎ ነበር ። አባይ ፀሃዬም ቀላል አይደለም ።እንደ ልደቱ ተንሸራታችነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ። ሳሞራም ቢሆን ከጀርባው ያለው ሃይል ቀላል አይደለም ።

የሃይለማሪያም ” ስሁል ሚካኤል ” ማነው? ይሄ ሰውዬ ራሱ ደክሞ እኔንም አደከመኝ ።እኔም ይሄው ” አፋልጉኝ? “እላለሁኝ። ሃበሻ ሲተረት “ሙት ወቃሽ አትሁኑ ” ይላል ። እኔም ዛሬ ሃይለማሪያም የተባለ ሙት ወቃሽ ሆንኩኝ መሰለኝ። ይቅር ይበለኝ! !

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: