The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

መልካም ሰው ሕያው ነዉ!

ፈቃደ ሸዋቀና

የጓደኛዬን የአቶ ፈቃደ ሸዋቀናን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የስማሁት በታላቅ ሐዘን ነዉ። የፈቃደ ሞት ለማመን የሚከብድ በጣም አስደንቃጭና አሳዛኝ ያልተጠበቀ ዱብ-ዕዳ መርዶ ወይም መርግ ሆኖ ይሰማኛል። ቁም ነገረኛ ጓደኛ፣ ምሁር አስተማሪ፣ የሰብአዊ መብት ጠበቃና የነጻነት ተከራካሪ የነበረው ፈቃደ ሸዋቀና የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብርና ነጻነቱን ተጎናጽፎ ለማየት የነበረዉ  ምኞት ዕዉን ሆኖ ሳያይ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ታላቅ ሐዘን ነዉ። በዚህ  አሳዛኝ ወቀት  እንደ ሻማ ቀልጦ ዕውቀትን በመዝራት ሙያዊ ግዴታዉን ስለተወጣዉ ምሁር፣ ሃላፊነት እንደሚሰማዉ ዜጋ ለሀገሩና ለወገኑ ድምጹን ከፍ አድርጎ ስለጮኸዉ የነጻነት አርበኛ ፈቃደ ሸዋቀና የሕይወት ጉዞና የትግል መስዋዕትነት መዘከር ከእኛ በሕይወት ካለነዉ ወዳጆችና የትግል አጋሮች ይጠበቃል።  ከዚህ እምነት በመነሳትም በቀብር ስርዓቱ ላይ ለመገኘት ሳልችል በመቅረቴ የሚሰማኝ ታላቅ ጸጸት እንዳለ ሆኖ፣ ከወጣትነት የትምህርት ቤት ጓደኝነት እስከ ጉልማሳነት በዘለቀዉ ግንኙነታችን ስለ እሱ የማውቀውንና  የሚሰማኝን ለወዳጅ ዘመድ በማካፈል ስዘክር በአክብሮት ሐዘን ነዉ።

የቅርብ ጓደኞቹ `ባላምባራስ` (ባባቱ የማዕረግ መጠሪያ) በሚል የቁልምጫ ቅጽል ስም እንጠራው ከነበረው ፈቃደ ጋር ትዉዉቃችን ከትምህርት ቤት ይጀምራል። ፈቃደ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ደብረሲና-አርማኒያ  ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፥ ኋላ ላይ ትምህረት ቤት ቀይሮ ስለመጣ ሁለታችንም በአቤቶ ነጋሲ ክርስቶስ ወረደ ቃል መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቢት ( መንዝ-ሞላሌ) በዘመነተኝነት (ኮንቴምፖራሪስ) በመሆን አብረን ተምረናል። በአንድ የክፍል ደረጃ ልዩነት ስምንተኛ ክፍል እንዳጠናቀቅንም በ960ዎቹ መጀመሪያ አጋማሽ ከተለያዩ የሰሜን ሸዋ አዉራጃዎች ይመጡ የነበሩ ተማሪዎችን እየተቀበለ ያስተምር በነበረዉና ደብረ-ብርሃን በሚገኘዉ የይለማሪያም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለሁለጥ ዓመታት አብረን ተከታትለናል። ዛሬ በሕይወት ካሉና ከሌሉ የጋራ ጓደኞቻችን ጭምር ለአንድ ዓመት በአንድ ግቢ ውስጥ በጉርብትናም በጓደኝነትም ኖርናል። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች በምንማርበት ወቀት በክፍል ደረጃ ብንለያይም  በእግርና  በመረብ ኳስ ሜዳዎች ኳስ እየረገጥን፣ የጠረንጴዛ ቴኒስና `ዳማ ` እየተጫወትንና እየተወዳደርን ጊዜ አሳልፈናል። ሁልጊዜም ተጨዋችና ደስተኛ የነበረዉ `ባላምበራስ` ፈቃደ `ሀርሞኒካ` የመጫወትና የማንጎራጎር ችሎታ ስለነበረዉ እያዝናናን መልካም የወጣትነትና የትምህርት ቤት ጓደኝነት አሳልፈናል።

ፈቃደ ትምህርት የመቀበል ተስጥዖና ችሎታው ከፍተኛ የነበረ ብቻ ሳይሆን፣ በዘመኑ ከሃይለማርያም ማሞ ኮከብ ተማሪዎች አንዱ ነበር ማለት ይቻላል። ይህም ችሎታዉ አስራ አንደኛ ክፍል ሲያጠናቅቅ ሌላ የተሻለ የትምህርት ተቋም እንዲገባ በር ከፍቶለታል። በንጉሱ ዘመን የልዑል በዕደ-ማርያም ትምህርት ቤት ይባል የነበረዉ ዝነኛ ትምህርት ቤት፣ በተለያዩ ክፍለ ሀገሮች ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች አስራ አንደኛ ክፍል ያጠናቀቁ  ጎበዝ ተማሪዎችን እየመለመለ ለአንድ ዓመት የመሰናዶ ትምህርት ይሰጥ እንደነበረ ሲታወቅ፣ ከኃይለማርም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ይህ ዕድል ከገጠማቸዉ ተማሪዎች መካከል ፈቃደ አንዱ ለመሆን በቅቷል። ባገኘዉ መልካም ዕድል ለአንድ ዓመት የተሰጠዉን የመሰናዶና የዩኒቨርሲት መግቢያ ትምህርት በሚገባ አጠናቆ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ችሏል። የ1966 የአብዮት `ፍንዳታን` ተከትሎ በታወጀዉ “የእድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዉ ሲዘጋ እንደማንኛዉም የከፍተኛ ትምህርት ተማሪ  ግዳጁን ለመወጣት ዘምቷል። ዘመቻዉ ሲቋረጥም በጊዜዉ የነበረዉ የፓለቲካ ትኩሳት ትምህርት የሚያስቀጥል መስሎ ስላልታየዉ በትምህርት ሚኒስቴር ተቆጥሮ ለተወሰኑ ዓመታት በሁለተኛ ደረጃ መምህርነት አገልግሏል።

የጀመረዉን ትምህርት ለመጨረስ በነበረዉ ፍላጎት በ1970ዎች  የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ አዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲ ተመልሶ ሲገባ፣ ከእኔም ጋር በዚሁ ካምፓስ ዉስጥ እንደገና ተገናኘን ጓደኝነታችንን ለመቀጠል ቻልን። የተለያዩ የትምህርት መስኮች የምንከታተል የነበረ ቢሆንም ከሌሎች ሁለት የጋራ ጓደኞቻችን ጋር በመሆን ለሁለት ዓመታት በአንድ የመኝታ ክፍል (ዶርም) ዉስጥ ኖረናል።  ምግብ ቤት አብረን ተስልፈን በልተናል። ሲጋራ እየተቀባበልን አጪሰናል። ከጥናት ወይም ከራት በኋላም ከግቢ እየወጣን  በአራት ኪሎ፣ ሰባ ደረጃ፣ ጃንሜዳና ሽሮ ሜዳ  መንገዶች የተለያዩ ፓለቲካዊና ማህበራዊ  ጉዳዮችን እያነሳን እየጣልን  በእግር ተንሽራሽረናል። ዩኒቨርሲቲውን ከለቀቅሁም በኋላም አገር ለቅቄ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ የጓደኝነት ግንኙነታችን ቀጥሏል። በነበረዉ ከፍተኛ ዉጤት ዩኒቨርሲቲዉ መርጦ ካስቀራቸዉ ወጣት ምሁራን መካከል አንዱ የነበረው ፈቃደ ወያኔ `በችሎታ ማነስ` በሚል ጠንጋራ የዘር ፓለቲካ ከስራዉ በግፍ አፍናቅሎት የስደትን ህይወት ከተቀላቀለ በኋላም በስልክና በኢሚል እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ግንኙነት ስናደርግ ቆይተናል።

ፈቃደ ብሩህና ፈጣን አእምሮ፣ ነገሮችን በቀላሉ የመረዳ የተፈጥሮ ተሰጥኦ፥ የማንንም መብት የማይጋፋ የራሱንም የማያስነካ፣ በራሱ የሚተማመን፣ ከትንሹም ከትልቁም መግባባት የሚችል፣ አዛኝና ርህሩህ፣ የተሟላ ሰብዕና ወይም ተክለ-ስዉነት የነበረዉ ሰዉ ነበር። ፈቃደ ቀልድና ጨዋታ አዋቂ፣ የደስታ ተካፋይ፣ በሐዘን ደራሽ፣ ሀሳብና ምክር ለጋሽ፣ በጎ አሳቢና በችግር ጊዜ አጽናኝ ነበር። ፈቃደ እንደ ምሁር ነገሮችን ከስሜት ነጻ ሆኖ ለማየት የሚሞክር፣ በዕዉቀትና በመረጃ፣ በምክንያትና በአመክኖ (ratinal and logical) የሚያይ፣በአስተሳሰቡ ነጻና በሳል፣ሐሳቡ ጥልቅ፣ (Independent, deep thinker and versatile) ነበር። ፈቃደ ሐሳቡን በንግግርም በጽሑፍም ማስተላለፍ የሚችል የተዋጣላት ተንታኝ ጸሐፈ (prolific writer) መሆኑን በተለያዩ ድረ-ገጾች በበተናቸው አስደማሚ መጣጥፎቹ ያስመሰከረ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቻችን ግንዛቤያችንን ለማዳበር ያስቻለን መሆኑን መካድ አይቻልም። እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊና ጥልቅ ግንዛቤ የነበረዉ፣ አገርና ወገን ወዳድ፣ የዘርና የጎጥ ፓለቲካ የሚጸየፍ፣ከጭፍን ወገነተኝነትና ጭፍን ጥላቻ የነጻ፥ ፍትህ፣ነጻነት እና እኩልነት የሰፈነባት፣ ሁሉም ዜጎችና ማህብረስቦች በእኩልነት የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ዕዉን እንድትሆን ምኞት የነበረዉ ብቻ ሳይሆን የራሱን ድርሻ ለመወጣት ይወጣ ይወርድ እንደነበር ወዳጅም ጠላትም የሚያውቀው ጉዳይ ነዉ።

ሆኖም ግን የተፈጥሮን ሕግ መሻር አይቻልምና ብዙዎቻችን ባላሰብዉነዉን ባልጠርጠርነዉ ወቅትና ሁኔታ ከእናት አገሩ እንደተለየ በስደት ዓለም  እስከወዲያኛው ተሽኘ። ባልተጠበቀዉ የሞት አደጋ ቤተሰቡ አለኝታ አባወራ፣ ወዳጆቹ ጓደኛ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም አንድ ተቆርቋሪና ታጋይ ልጁን አጥተዋል። ይሁን እንጂ ሞት የተፈጥሮ ህግ ሆኖ በአጸደ ሥጋ ቢለየንም የመልካም ሰዉ ስምና ታሪክ ከመቃብር በላይ ነዉና፥ የፈቃደ መልካም ስምና ተግባርም ህያዉ ሆኖ በትዉልድ ሲዘከር ይኖራል። ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ ዘመዶቹ ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁ። ቸሩ እግዚአብሔር ነፍሱን በገነት ያኑራት!!!።

 

ሕይወት እንደዚህ ናት??

አዎ፣ ሕይወት እንደዚህ ናት፣

ብልጭ ብሎ ድርግም፣አለሁ ሲሉ ጥፍት፣

እንደ ጸሐይ ወጥቶ፣ እንደ ሻማ መጥፋት፣

ሀሳብ ከግብ ሳይደርስ፣ ሳይቋጭ ምኞት፣

እመጣለሁ ሲሉ፣ ወጣ ብሎ መቅረት፣

እንደ አበባ ፈክቶ፣ እንደ ጤዛ መርገፍ፣

ደህና ሁን ፈቃደ፣ በል እንግዲህ እረፍ።

ሆኖም ግን አምናለሁ !!!

ፈቃደ አትረሳም፣ እስከ ዘላለሙ፣

ተጽፏል ታሪክህ፤  አይለቅም ቀለሙ።

አንተ የሕዝብ ልጅ፥ አፈሩ ይቅለልህ፣

በሥጋ ብትሞትም፥ በመንፈስ ሕያዉ ነህ።

ኃይለማርያም ለገሰ

hailelegesse@gmail.com

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: