The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ከፍሬያቸው አወቅናቸው!!!

K. Teshome

ሰኔ 2009

ዛፍ፣ እጽዋት እና አዝእርት ፍሬ እንደሚያፈሩ ሁሉ ድርጅትም ፍሬን ያፈራል:: የድርጅት መልካም ፍሬዎች የሚባሉትም ማልካም አስተዳደር፣ ዲሞክራሲ፣ በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ ወዘተ ናቸው:: የዛፍ፣ እጸዋት፣ አዝእርት ፍሬዎች ሁኔታ የሚወሰነው በአፈሩ ንጥረ ነገር ፣ የአየር ንብረቱ ሁኔታ ፣ ሙቀትና የጸሀይ ብርሀን እና በሚያገኘው ውሃ እንደሆነ ሁሉ የአንድ ድርጅት ፍሬ የሚወሰነውም ድረጅቱ ውስጥ ባለው የሰው ሁኔታ፣ ፖሊሲ፣ ገንዘብ እና ቁሳቁስ ነው:: የዛፍ መልካምነቱ  በፍሬው ይታወቃል የሰውም መልካምነት በንግግሩ እና በምግባሩ ይገለጣል እንደሚባለው ሁሉ የአንድ ድርጅትም መልካምነት በግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ ህይዎት ላይ በሚያደርገው ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ ግንባታ ነው:: በዚህች አጭር ጽሁፌ አሁን ሃገራችንን እያስተዳደረ ያለው ወያኔ/ኢሃደግ የተባለው ድርጅት  ካፈራቸው ፍሬዎች አንዱ የሆነውን  ዘረኝነት ነው::

የሀገሬ ሰው ደርግ ተብሎ  የሚጠራው ድርጅት ፍሬው መራራ ስለሆነበት ያለ የሌለ አቅሙን አሰባስቦ በገዘገዘው እና  ባዳከመበት ወቅት ወያኔ የተባለው ታጣቂ ድርጅት ከበረሀ ወጥቶ አጋጣሚውን በመጠቀም በትረ ስልጣኑን በሃይል ነጥቆ ወሰደ:: ሁላችሁም እንደምታውቁት ወያኔ በተረ ስልጣኑን ሲይዝ ምን አልባት መከላከያ  በሚባለው ቀንዱ የመዋጋት አቅም ካልሆነ በስተቀር ታላቁን የኢትዮጵያን ህዝብ የማስተዳደር አቅምም አልነበረውም:: በሰው ኋይሉም፣ ባስተዳደር እውቀቱም ሆነ ልምዱ፣ በፖሊሲውም ፣ በፖለቲካውም  ያልበሰል እና እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: ዘረ ከልጓም ይጠቅሳል እንደሚባለው አዲስ አበባ ቤተ መንግስት ላይ ተቀምጦ ህዝብ አስተዳድራለሁ እያለ ሃሳቡ እና ምግባሩ ግን ያው የበረሀ ማንነቱን የሚያንጸባርቅ ነበር:: በዚህም የተነሳ ሃገሪቱ በግምት ስትመራ ቆይታለች::

በወያኔ ዙሪያ እና ላይ ተንጠላጥለው ያሉ ሰዎችም አይዞዋችሁ ወያኔን በትዕግስት ጠበቁ ሲጠነክር የዲሞክራሲ ካባ ትለብሳላችሁ፣ የዲሞክራሲ ጫማ ትጫማላችሁ፣ በብሄርተኛ ዲሞክራሲ ልጥ አንድ ትሆናላችሁ፣ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ትተነፍሱ የነበራችሁ ኦክስጅን ትተነፍሳላችሁ፣ ራባችሁ በጥጋብ፣ ጥማችሁ በርካታ ይሻራል እያሉ ለህዝቡ ተስፋ ሲሰጡ ዘመናት አለፉ :: የሃገሬም ሰው በዚህ የተስፋ ቃል አምኖ እና ተስፋ ሰንቆ “ በለስዋን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል” የሚባለውን ተረት እየተረተ የወያኔን መልካም ፈሬዎች ይጠባበቀ ነበር:: ከጊዜ ጊዜ ህዝቡ ወያኔ ወደፊት የሚያፈራቸው ፍሬዎች መልካም አለመሆናቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች ቢያይም እና ስድስተኛው የስሜት ህዋስ ጥርጣሬ ቢፈጥርበትም የሀገሬ  ሰው ግን ለማመን የማይቸገር ስለሆነ የወያኔን የተስፋ ፍሬዎች ትእግስትን ገንዘብ በማድረግ ለብዙ አመታት ሲጠብቅ ቆይቷል:: ወያኔ ግን አድሮ ቃሪያ መሆኑ በተደጋጋሚ ይታይ ነበር::

ከብዙ አመታትም በኋላ ወያኔ የተባለው ድርጅት ሌሎችን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተቋማት በማንቋሸሽ እና ሽባ ካደረዳቸው በኋላ እራሱን በፖለቲካ፣ በአደረጃጀት፣ ኢኮኖሚ እያጠነከረ መጣ:: መከላከያ የተባለ ቀንዱም ጠነከር፤ እንዳውም ፊደራል ፖሊስ የተባል እሾህ አወጣ:: ወያኔም የማይታዘዙትን እና የሚቃወሙትን ሁሉ በእሾሁና እና በቀንዱ እያስፈራራ እና እየተዋጋ አፍ ማስያዝ ጀመረ::

ቆይቶም ወያኔ የተባልው ድርጅት ብዙ ክፉ ፍሬዎችን አፈራ፦ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ሙስና፣ ትዕቢት፣ ውሸት ወዘተ የሚባሉ ፍሬዎችን::  የወያኔ አባዋራዎችም የዘረኝነት ፍሬን ከበሉ በኋላ ለኦህደድ፣ ብአዴን ወዘተ ሰዎች አበሉዋቸው:: እነርሱም በተዋረዳቸው በቴሌቪዠን፣ ሬድዮ፣ ጋዜጦች እና ስብሰባ መድረኮች ላይ ደግሰው ለካድሬዎቻቸው እና ለህዝቡ መገቡት:: የወያኔ ሰዎችም የዘረኝነትን ፍሬ ሲመግቡን መብታችሁ ይከበራል፣ ዲሞክራሲያዊ ትሆናላችሁ፣ የራሳችሁንህዝብ ትመራላችሁ፣ የራሳችሁን  እጣ ፈንታ  ትወስናላችሁ በሚል መሸንገያ እና ማታለያ ቃል በመጠቀም ነበር::አይጥ መብላት በምትፈለገው ምግብ እንደምትጠመድ ሁሉ እኛንም  የወያኔ ሰዎች በምንፈልገው ዲሞክራሲ ስም አጠመዱን::

መራራ የሆነው የዘረኝነት ፍሬም በዲሞክራሲ ተለውሶ የተሰጠን ስለነበር አፍ ላይ ጣፋጭ እና ልብን የሚያስደስት ነበር:: ቀስ በቀስ ግን የሚያሰክር፣ ማስተዋልን የሚነጥቅ፣ አእምሮን የሚያሳጣ እርስ በእርሳችንም እስከ አለመተዋወቅ ያደረሰ፣ እኛ የመባባል ባህላችንን ደፍጥጦ አንቺ፣ አንተ፣ እናንተ መባባልን የፈጥረ ሁኑዋል:: እኛም የዘረኝነትን ፍሬ ከበላን ጊዜ ጀመሮ አያቶቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን ካቆዩልን የአንድነት ትልቅ ክብር ተለየን፣ እርስ በእርሳችንም እስከ አለመተዋወቅ ደረስን:: የስካር ደረጃው የተለያየ አይደል! አንዳንዶቻችን እማ በዘረኝነት ፈሬው በጣም ሰለ ሰከርን በእማማ ኢትዮጵያ ስም መጠራትን አንፈለግም::

ሰው የዋጠውን ይተፋል፤ ያነበበውን ይናገራል እንደሚባለው ሁሉ እኛም አሁን የዋጥናትን የዘረኝነት ፍሬ በንግግር እና በትግበራ እየተፋናት በአለንጋዋም  እየተገረፍን  እንገኛለ:: እነሆ ዘረኝነት ለወያኔዎች  ስልጣን ማራዘሚያ ለእኛ ግን የድህነት፣ የጭቆና፣ አለመግባባት፣ እርስ በእርስ መለያያት እና ለተለያዩ መከራዎች አጋልጦናል:: እንዳውም አሁን አሁን እማ በዘረኝነት የመረዙን ወያኔዎች ሁቱ እና ቱሲ የበሉትን የዘረኝነት ፍሬ ካበሉን በኋላ በሁቱ እና ቱሲ መልሰው ያስፈራሩናል:: ለህጻን ልጅ የሚያስፈራራ መጫዎቻ ገዝቶ ሲጫዎት እንደገና በመጫዎቻው ማስፈራራት እንደ ማለት ነው:: አማራ እና ኦሮሞ  እሳት እና ጭድ ናቸው እስከ ማለት ያደረሳቸው የዘረኝነት እጀንዳቸው ነው:: እስቲ ዘረኝነት በተግባር ያመጣብንን የተወሰኑ አመላካች ጣጣዎች እናንሳ::

 

በደቡብ ኢትዮጵያ ጉራፈርዳ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ በሚባሉ አካባቢዎች የተሰማው የአደጋ ደወል ድምጽ የዘረንነት ፍሬ አይደለም?

ብዙ ቁጥር ያላቸው በጉራፈርዳ ይኖሩ የነበሩ ግብር ከፋይ አማርኛ ተናጋሪዎች በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሚመራው የክልል መንግስት ጫካ አቃጠላችሁ በሚል ሰበብ አገራችሁ ተመለሱ የሚል ዘር–የማጥራት ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል :: ከጉራፈርዳው ዘር– ማጥራት ወንጀል በተጨማሪ  በመጠኑ የላቀ እና በአይነቱምየከፋ ብዙ ሺ አማርኛ ተናጋሪዎችን ያፈናቀለ ዘር–ማጥራት በቤንሻንጉል–ጉምዝ ተደገመ። በዚኽን ጊዜ የፌደራሉ መንግስት ምንም እርምጃ ሲወሰድ አላየንም:: ይህ የሚያሳየው የመንግስት አጀንዳ ዘረኝነት መሆኑን ነው::

በኦሮምያ እና አማራ ክልል ያሉ ህዝቦች መብታችን ይከበር፣ በዘራችን ምክንያት የምንናቅ እና የምንሰደብ መሆን የለብንም፣በሃገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ልንቆጠር አይገባንም፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን አለብን ብለው ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መልኩ ሰላማዊ ተቃውም በማሰማታቸው ብቻ ወያኔዎች ጦርነት አውጀው ብዙዎቹ በአደባባይ በጥይት ተገድለዋል፣ በመቶ ሺዎቹ የሚቆጠሩ ታስረዋል፣ ድብደባ እና ሌሎች ሰቆቃዎች ደርሰውባቸዋል:: ለኦሮምያ እና አማራ ህዝብ መብት መከበር በሰላማዊ እና ህገ መንገስቱ በሚፈቅደው መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አባሎቻቸው በወያኔ ካድሬዎች እየተያዙ በአሸባሪነት፣ አመጽን በማነሳሳት፣ መንግስትን በሃይል በመገልበጥ ወንጀል ተከሰዋል:: የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፓርቲ አመራር የሆኑት እነ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና እና በቀለ ገርባ አሁን እስር ቤት ያሉት ወንጀል ሰርተው ሳይሆን በዘራቸው እና በፖለቲካ አመለካከታቸው ነው:: ታዲያ ይህ የዘረኝነት አይደለም?

የምናየው በአንድም ሆነ በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል ውስጥ ያለው ፍጥጫ፣ መቃቃር፣ መገዳደል፣ ጥላቻ የወያኔ የዘረኝነት ሴራ ውጤት ነው:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሁለት ሲኖዶሶች እየተመራች ትገኛለች:: አንዱ የሃገር ቤት ሌላው የውጩ ሲኖዶስ እየተባል:: ይህ የሆነው የቤተክርስቲያኒቱ ስርአት በማይፈቅደው ሁኔታ አሁን ከሃገር ውጪ ያሉት ፓትሪያሪክ ከመንበራቸው በወያኔ መሪዎች በግዳጅ እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ ከራሳቸው ወገን የሆነውን  ፓትሪያሪክ በመሾማቸው ነው::  በጅማ፣ በአርሲ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል ግጭትን በመፍጠር ብዙ ህይዎት እና ንብረት የወደመው በወያኔ የዘረኝነት ሴራ ነው::

በታሪክ አይተነው ሰምተነው በማናውቀው ሁኔታ በካርታ ላይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ራስ ደጀን ተራራ ወደ ትግራይ የገቡት፣ የትግራይ ክልል የጎንደርንና ጎጃምን መሬት ቆርጦ ቤኒሻንጉል ክልል ጋር ድንበርተኛ የሆነው በወያኔ የዘረኝነት ተንኮል ነው::

በየቢሮዎቻችን አዳዲዲስ አለቆች ተሹመው ሲመጡ ሰለ እነርሱ መጀመሪያ ማዎቅ የምንፈልገው ስለ ምናቸው ነው? የአመራር ብቃታቸውን? የትምህርት ደረጃቸውን እና ልምዳቸውን ? ወይንስ ዘራቸውን? ብዙዎቻችንን  የሚያስማማን አንድ መልስ ይመስለኛል እርሱውም ዘራቸውን የሚለው ነው:: ይህ ታዲያ ዘረኝነት አይደለምን? እንዲህ እንድናስብ ያደረገን የወያኔ የዘረኝነት ፍሬ ነው::

ከደርግ ዘመን በእጅጉ በተቃረነ ሁኔታ ሀገራችን ሙስና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰባቸው ሃገሮች ተርታ ናት:: በወያኔ  የአገዛዝ ዘመን እስካሁን ከ30 ቢሊዮን ዶላር ባላይ ከሀገር ወጥቷል:: በ 2009 ዓም እንኳን  በ3 ወራት ውስጥ ከ 3 ቢሊዮን ዶላሮች ባላይ ከሀገራችን ወጥቷል:: ማነው ኦሮሞ ባለስልጣን  ከትግሬው ጋር ሙስና የሚሰራ፣ ማነው አማራ ባለስልጣን ከኦሮሞው ጋር የሚሰርቀ:: የወያኔ ባለስልጣናት በዘር፣ በጎጥ፣ በአካባቢ ልጅነት እየተሸፋኑ እና እየተደባበቁ ነው የህዝብን ንብረት የሚዘርፉት::

በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ላይ የተሰሩ ህንጻዎች ባለቤትነታቸው የማን ነው? የትግራይ ተውላጆች እንደምትሉኝ አልጠራጠርም:: ትክክልም ናችሁ፤ ይህ የአደባባይ ሚስጢር ስለሆነ:: ይህ የሆነው አማራው፣ ኦሮሞው ወይንም የሌላው ብሄር ተውላጆች ህንጻ መገንባት ስለማይችሉ ሳይሆን እነዚህ አይነገብ የሆኑ ቦታዎች ለእነርሱ ስለማይሰጣቸው ነው:: እነዚህ ቦታዎቸ በአብዛኛው ለትግራይ ተወላጆች ብቻ መባዎች ናቸው:: ታዲያ ይህ የዘረኝነት ፍሬ አይደላም?

ይህ የዘረኝነት መንፈስ እና መለያየታችን በዚሁ ከቀጠለ የወያኔ መንግስት አብዝቶ በጂራፍ እየገረፈን፣ በጥይት እየቆላን ግዛቱን ያጸናብናል፣ በብራት አለንጋም ይገርፈናል::

ስለዚህ ህዝባችን እንደ እኔ ሁለት አማራጭ አለው ብየ አምናለሁ::  ህይውት ምርጫ ስለሆነ ከሁለት አንዱን መርጦ መኖር ያስፈልጋል:: አንደኛው በሃገራችን ባእድ እና ባሪያዎች ሁነን መኖር:: ምርጫችን ይሄ ከሆን ደግሞ አፋችንን ሸብበን፣ ሲያስሩንም፣ ሲገድሉንም እንደሚታረድ በግ ሁነን መኖር:: እነርሱም እርስ በእርሳችንን እያናከሱን፣ እያጋጩን እና እያጋደሉን ይኖራሉ:: እኛን በዘረኝነት ማህረብ ጨፍነው ያለንን ሁሉ ከወሰዱ በኋላ ሃገራችንን በታትነዋት በስልጣንም ማርጀት ስለማይቀር ሲያረጁ ስልጣን ለቀው ይሄዳሉ::

ሁለተኛው ደግሞ እስካሁን እሺ ብለናቸው ለውጥ ስላልመጣ ኢትዮጵያዊ የአንድነት መንፈሳችንን ይዘን ለውጥ ለማምጣት  መጣር:: ከወያኔ ካደሬዎች ውጪ ያላችሁ ሰዎች ይህን አማራጭ እንደምትመርጡ አያጠራጥርም:: ምርጫችን ይህ ከሆነ ደግሞ ምንም እንኩዋን የዘረኝነት እና መለያየት ዋና ምክንያት ወያኔ ቢሆንም ሰው የችግሩ ፈጣሪ ነው እንደሚባለው ሁላችንም በተለያዩ ደረጃዎች አሁን ላለንበት ችግር ድርሻ አላለን ማለትም በግለሰብ፣ በቡድን፣ በማህበረሰብ እና  በተቋም ደረጃ ለችግሩ አስተዋጾ ያደረግን ስለሆነ ሁላችንም የችግሩ አካል ሁነን ልንሰራ ይገባል:: ስለሆነም በተለያዩ ደረጃዎች ምን ምን ስራዎች ሊከወኑ እንደሚገባ የማምንበትን ነገረ እንደሚከተለው አስቀምጫሁ::

በግለሰብ ደረጃ ፦ ብዙዎቻችን ሳናውቀው የወያኔ ተልዕኮ ማስፈሚያ ሁነናል ብየ አምናለሁ:: እንደ ግል እያንዳንዱ በዘረኝነት መርዝ ሃሳቤ፣ ንግግሬ እና ምግባሬ ተበክሉዋል ወይ በሎ መጠየቅና እራስን ማስተካከል፣ በዘረኝነት አስተሳሰብ ፋንታ አእምሮዋችን ጸረ ዘረኝነት አስተሳሰብ እንዳስብ ማስለማድ፣ ምላሳችን አንድነትነን እና ፍቅርን የሚሰብክ፣ምግባራችንም አንድነትን የሚገልጥ ሊሆን ይገባል:: እያንዳንዱ ግለሰብ ከተስተካከለ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ነገድ ፣ ጎሳ እና ሀገር ይስተካከላል:: ሌላው እራሳችንን የዘረኝነት ቫይረስ ከለከፋችው እና ዘረኝነትን ከሚያራምዱ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና ሚዲያዎች  ማራቅ ይገባል:: ቢቻል እነዚህ አካላትን ማንቃት ሳያውቁት ለወያኔ የከፋፍለህ ገዛው ፖሊሲ ባንዳ ሁነዋልና:: እነዚህ አካላት ለወያኔ አገዛዝ ህልውና በመሆን የህዝብን መከራ ያራዝማሉ እንጂ መለያየትን እየሰበኩ ለውጥ አያመጡም:: “አንድነት ሀይል ነው” እና “እርስ በእርስዋ የተለያየች መንግስት አትጸናም” የሚለው መልእክት አልገባቸውምና::

ሁለተኛ ከወያኔ የአገዛዝ ቀንበር ውጪ የሆኑ የህዝብ ልሳንናት ሚዲያዎች እንደ ኢሳት ሬድዮና ቴሌቪዥን ፣ የአሜሪካ ድምጽ  የአማረኛ ሬድዮ፣ የጀርመን ድምጽ የአማረኛ ሬድዮ፣ ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ እና ሌሎችም የወያኔ ልሳናት የሆኑ ሚዲያዎች የሚዘሩትን የዘረኝነት እና የመለያየት አስተምህሮ ሊመክቱ ይገባል:: አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብን ሊሰበኩ እና ሊያስተምሩ ይገባል::

ሶስትኛ ከክፉ ዛፍ ስር ምሳር አለ ዛፉም ይቆረጣል ፍሬው መራራ ነውና  እንደሚባለው  በዋናነት ዕፀ ዲሞከራሲ፣ ዕፀ ነጻነት፣ ዕፀ አንድነት ፍሬ ይሰጠናል ብለን ከካጫካ መጥቶ ቤተ መንግስት ሲገባ ዝም ያልነው ወያኔ በዲሞክራሲ ሲያጭበረብር ቆይቶ ወደለየለት ዘኝነት፣ ኢ-ዲሞከራሲያዊነት እና ጭቆና ስለተቀየረ፣ ህዝቡን ቀንድ እና እሾህ በሆኑ መካላከያ እና ፖሊሶቹ እያስፈራራ እና እየገደለ ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በፊት በደርግ እንዳደረገው ሁሉ የወያኔን አገዛዝ ተባብሮ መጣል ነው:: ይህ ከሆነ እኛ ከዘረኝነት መርዝ የምንፈወሰ እና የምንነጻ መልሰን አንበከልም ፤ የወደፊቱንም ትውልድ ከዘረኝነት አባዜ ታድገን ሀገራችን ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ እንችላለን::

በአራተኛ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎጠኝነትን ማራመድ ትተው ህብረ ብሄራዊነትን ገንዘብ ቢያደርጉ:: በ1997 ዓም  በተደረገው ምርጫ ቅንጂት ምርጫ አሸንፎ የነበረው ብሄረተኛ ሳይሆን ብሄራዊ ፓርቲ ስለሆነ ነው ብየ አምናልሁ:: የፖለቲካ ፓረቲዎች ህዝቡን አንድነት ሊሰብኩ ቢችሉ:: እኔ ይገርመኛል አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች እንኳን ሀገራዊ ራዕይ ጠንከር ያለ እንኳን አካባቢያዊ ራዕይ የላቸውም:: አንዳንዶቹ ፖለቲካን ድህረ ጡረታ ስራ አድረገው ስለቆጠሩት ሳይለወጡም ፣ ሳይለውጡም የለውጥ እንቅፋት እና አሰተጓጓይ ሁነው ይታያሉ:: ወያኔም እንደ ባንዳነት የሚጠቀምባቸው እነዚህን ነው:: እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ድርጅቶች ሊጠፉ ይገባል:: በምትኩ ብሄራዊ ራዕይ ያላቸውን ድርጆቶችን መደገፍና ማጠናከር መልካም ነው በዬ አምናለሁ::

በአምስተኛ ደረጃ የሃይማኖት ተቋማት ከፖለቲካ ገለልተኛ ሁነው ከህዝቡ ጋር ቅርበት እና ተቀባይነት ስላላቸው የእምነቱ  ተከታዮችን ስለ አንድነት፣ ፍቅር እና  ሰላም አጠናክረው መስብክ ቢችሉ:: ከዚህም አልፎ ዘረኝነት እንደ አንድ የመወያያ አጀንዳ ተይዞ መድረክ ተዘጋጅቶለት ውይይት ማድርግ ተገቢ ነው:: ቤተ እምነቶችም መንግስት የሀይማኖት ተቋማትን እየተጠቀመ የሚዘራውን የዘረኝነት ጥፋት ስራ እምቢ ሊሉ ይገባል:: እንድዚህ ሲሆን ነው ወያኔ የኢኮኖሚ፣ ፍትህ፣ ትምህርት፣ማህበራዊ፣ የፖለቲካ እና የባህል ተቋማትን እየተጠቀም የሚዘራውን ዘረኝነት መቋቋም የሚቻለው::

posted by Gheremew Argahw

Single Post Navigation

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: