The time for change

No bullet can stop the spirit of justice and democracy!!!

ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልና የባህር በር ጥያቄ የተካተቱበት ረቂቅ የፖለቲካ ድርድር አጀንዳ ቀረበ

17 Jun, 2017 By ዮሐንስ አንበርብር (Reporter)

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና 16 ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ድርድርና ውይይት ለማድረግ በተስማሙት መሠረት፣ የሕገ መንግሥቱ የተለያዩ አንቀጾችን ከማሻሻል አንስቶ እስከ የባህር በር ጥያቄ የተካተተበት 13 ነጥቦችን የያዘ ረቂቅ አጀንዳ ለውይይት ቀረበ፡፡

የድርድርና የውይይት አጀንዳዎቻቸውን ኢሕአዴግን ጨምሮ 17 ፓርቲዎች ለድርድር መድረኩ የሙያና የጽሕፈት አገልግሎት ድጋፎችን ለሚያቀርበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ካቀረቡ በኋላ፣ ፓርቲዎቹ ባዋቀሩት አጀንዳ አደራጅ ኮሚቴ ተጠናቅረውና ቅርፅ ይዘው እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሠረት 13 ጥቅል ርዕሶችን የያዘ ረቂቅ የመወያያ አጀንዳ ተቀርፆ ረቡዕ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ሁሉም ፓርቲዎች በተገኙበት ለውይይት ቀርቧል፡፡

በቀዳሚ አጀንዳነት የቀረበው የምርጫ ሕጎችን ለማሻሻል የተቀመጠው አጀንዳ ነው፡፡ በውስጡም የምርጫ ሕጉን፣ የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅንና የፓርቲዎች ሥነ ምግባር አዋጅን በውስጡ አካቷል፡፡ በዚህ ውስጥ ስለአገር አቀፍ ምርጫ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው አንቀጽ አልተካተተም፡፡

ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል በሚለው ሌላ አጀንዳ ሥር የሕገ መንግሥቱ የተለያዩ አንቀጾች እንዲሻሻሉ በመቅረባቸው በንዑስ አጀንዳነት ተይዘዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንቀጽ 39፣ 40፣ 47፣ 72(3) ይገኙበታል፡፡

ሌሎች አዋጆችን ማሻሻል በሚለው ዓቢይ አጀንዳ ሥር ደግሞ የፀረ ሽብር ሕጉ፣ የብዙኃን መገናኛና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና ታክስ አዋጆችና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በንዑስ የድርድር አጀንዳነት ቀርበዋል፡፡

ብሔራዊ መግባባት፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ጉዳይ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን መከተል እንዳለባቸው፣ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን መፍጠር፣ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድንበርን መወሰን (በውስጡ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እንደተካተተበት ተገልጿል) በዓቢይ አጀንዳነት የተረቀቁ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የክልሎች ድንበር አከላለል፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አወቃቀር፣ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋን የተመለከቱ ዓቢይ አጀንዳዎችም ይገኘብታል፡፡ ፓርቲዎቹ ቀደም ባለው ውይይታቸው ድርድሩ የሚመራበትን ደንብ ማፅደቃቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ደንብ መሠረት በአደራዳሪነት መድረኩን የሚመሩት ከራሳቸው ከፓርቲዎቹ በዙር የሚመረጡ እንዲሆኑ ስምምነት ተደርሶ በሥነ ሥርዓት ደንቡ ተካቷል፡፡

ይህንኑ በመከተልም ለዕለቱ የተመረጡ አደራዳሪዎች በቀረበው የድርድር አጀንዳ ላይ ውይይት እንዲጀመር መድረኩን ከፍተዋል፡፡ መድረኩ ለውይይት ክፍት ከተደረገ በኋላ ከውይይት ይልቅ ንትርክ መባል የሚችል አተካራ እስከ ቀትር ድረስ ተስተውሏል፡፡

የንትርኩ መነሻ የተወሰኑ ፓርቲዎች ያቀረቧቸው የድርድር አጀንዳዎች ውድቅ እንደተደረገባቸው ለመግለጽ የተጠቀሙባቸው ጥርጣሬ አዘል ንግግሮች ናቸው፡፡ በመድረኩ የተሰየሙትን አደራዳሪዎች መጠራጠር፣ ፈቃድ ሳያገኙ ንግግር ማድረግና እንዲያቆሙ ሲጠየቁ የውይይት መሪዎቹን አለመስማት ተሰማርተዋል፡፡

በዚህ አተካራ ውስጥ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ተሻለ ሰብሮ ትኩረት በመሳብ ግንባር ቀደም ነበሩ፡፡ አቶ ተሻለ ሙግት ውስጥ የገቡት ፓርቲያቸው ካቀረባቸው ከ30 በላይ የድርድር አጀንዳዎች ውስጥ ተቀባይነት አግኝተው የቀረቡት 13 ብቻ ናቸው የሚል ምክንያት ይዘው ነው፡፡

ለአብነት ያህል ካነሱት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ የንግድ ድርጅቶች ጉዳይ አልተካተተም የሚል ይገኝበታል፡፡ አጀንዳ አደራጅ ኮሚቴ ከነበሩት ሦስት የፓርቲ ተወካዮች መካከል የእርሳቸው ፓርቲ የተወከለ ሲሆን፣ አጀንዳዎችን በማደራጀት ሒደት ውስጥ በሦስቱ ተወካዮች መካከል ልዩነት እንዳልነበረ ቀሪዎቹ ሁለት ተወካዮች በወቅቱ ተናግረዋል፡፡ የራዕይ ፓርቲ ተወካይ የኮሚቴው አባል ግን ልዩነት እንደነበር በውይይቱ ወቅት ጠቁመዋል፡፡

የአጀንዳ አደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አጀንዳዎቹ የተለዩበትን ሒደት አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በዋነኝነትም ከሦስት በላይ በሆኑ ፓርቲዎች በድርድር አጀንዳነት የቀረቡ ሐሳቦች ተለይተው መደራጀታቸውን አብራርተዋል፡፡ የሚመጋገቡ ነጥቦችን በማግባባት መጠናቀሩንም ገልጸዋል፡፡

ከሦስት በታች ፓርቲዎች የቀረቡ የውይይት አጀንዳዎችን ያቀረቡ ፓርቲዎች፣ ኢሕአዴግ በሰጠው አስተያየት መሠረት የሁለትዮሽ ድርድር ማድረግ እንደሚችሉ በመግለጹ አለመካተታቸውን አብራርተዋል፡፡

የራዕይ ፓርቲ ሊቀመንበር ያነሱት የፓርቲ የንግድ ድርጅቶች ጉዳይ ውድቅ አለመደረጉን የአደራጅ ኮሚቴው አባልና የኢሕአዴግ ተወካይ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ገልጸዋል፡፡ ይህ ጉዳይ የምርጫ ሕጎችን ማሻሻል በሚለው ርዕስ ሥር በተዘረዘሩት ንዑስ ነጥቦች ማለትም በፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ የተሸፈነ በመሆኑ የድርድሩ አካል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፖሊሲ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የድርድር ጥያቄዎች ውድቅ መደረጋቸውን አቶ አስመላሽ ተናግረዋል፡፡ በሰጡት ምክንያትም በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ድርድር ማድረግ ትርጉም እንደማይሰጥ፣ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ድርድር ሳይሆን ውድድር ትክክለኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማብራሪያዎች የቀረቡ ቢሆንም ንትርኩ ግን ሊቆም አልቻለም፡፡

ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ያረቡት አጀንዳ ያላግባብ ውድቅ እንደተደረገባቸው ማቅረብ ቀጥለዋል፡፡ መላው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ተሰማ ሁንዱማ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነቱን በሕዝበ ውሳኔ እንዲያስከብር ፓርቲያቸው በአጀንዳነት ቢያቀርብም አለመካተቱን በመጥቀስ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብን የሚወክለው ገዳ የተባለ ፓርቲ በበኩሉ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው የአገሪቱ መጠሪያ ስም ‹‹የኩሽ መሬት›› በሚል ስያሜ እንዲቀየር ያቀረበው የድርድር ነጥብ አለመካተቱን በመጥቀስ ክርክር አቅርቧል፡፡

በውይይቱ ማብራሪያዎች ከተሰጡ በኋላ ንትርኩ መቀጠሉ ግራ እንዳጋባቸው የገለጹት የኢሕአዴግ ተወካይ የቀድሞው ትምህርት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ‹‹ወደዚህ ውይይት እስክንገባ አሥር በሚሆኑ ውይይቶች ሥነ ሥርዓት ተከትለን የሰከነ ውይይት አድርገናል፡፡ ዛሬ በድንገት ነገሮች ፈር የሳቱት ለምንድነው? የውጭ ታዛቢዎች ስላሉ ነው?›› ሲሉ ምፀታዊ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በዕለቱ የተካሄደውን ውይይት በታዛቢነት እንዲከታተሉ ጥሪ ከተደረገላቸው የውጭ ታዛቢዎች መካከል በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመንና የካናዳ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ ከአገር ውስጥ በታዛቢነት የተጋበዙ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክና የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ ድርድሩ የሚመራበትን ደንብ ታዛቢዎች ከመታዘብ ወጪ ሐሳብ መሰንዘር እንደማይችሉ፣ ለመገናኛ ብዙኃንም ስለድርድሩ አስተያየት እንዳይሰጡ ይገድባል፡፡ ይሁን እንጂ በዕለቱ የነበረውን ረብ የለሽ ንትርክ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች በጉርምርምታ ለመገሰጽ ሞክረዋል፡፡

አቶ ሽፈራው በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ‹‹የኩሽ መሬት›› በሚለው የመደራደሪያ አጀንዳ ላይ ኢሕአዴግ ለመደራደር ሥልጣን እንደሌለው፣ በተመሳሳይም የኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት በሕዝበ ውሳኔ እንዲለይ በቀረበው ነጥብ ላይ ኢሕአዴግ እንደማይደራደር ገልጸዋል፡፡ የመደራደሪያ አጀንዳዎቹን ያቀረቡት ፓርቲዎች በራሳቸው መንገድ ማስፈጸም እንደሚችሉ አቶ ሽፈራው አክለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ንትርኮቹ መስከን በመቻላቸው የቀረቡትን 13 ረቂቅ አጀንዳዎች አንድ በአንድ ወደ ማፅደቅ ሒደት ተገብቷል፡፡

ኢሕአዴግን ከወከሉት መካከል አቶ ሽፈራው የፓርቲውን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኢሕአዴግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለድርድር እንደማይቀመጥ ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ አሁንም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆና በዚህ ጉዳይ ላይ መደራደር እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የንግድ ሕጉን የማሻሻል ሥራ በሒደት ላይ በመሆኑ መደራደር ሳያስፈልግ፣ ፓርቲዎች በማሻሻል ሒደቱ ተሳታፊ እንደሆኑ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ቁጥር አንድ አጀንዳ ሆኖ የቀረበውን ምርጫ ሕጎችን ማሻሻል የሚለውን አጀንዳ ኢሕአዴግ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀበለው፣ እንዲሁም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የቀረበውንም እንደሚቀበለው ገልጸው፣ በሌሎቹ ላይ ድርድር እንዲደረግ ፓርቲዎቹ የፈለጉበትን ምክንያት ካብራሩ በኋላ ኢሕአዴግ አቋሙን እንደሚያሳውቅ ገልጸዋል፡፡

በሰጡት ማብራሪያ መሠረት የምርጫ ሕጎችን ማሻሻል የሚለው ቁጥር አንድ አጀንዳ ተቀባነት አግኝቶ እንዲያልፍ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፡፡

በቁጥር ሁለት አጀንዳ ሥር የተዘረዘሩ አዋጆች (ፀረ ሽብር ሕጉና የመሳሰሉት) እንዲሻሻሉ የጠየቁ ፓርቲዎች ምክንያቶቻቸውን ከዘረዘሩ በኋላ፣ የኢሕአዴግ ተወካዮች የፓርቲያቸውን አቋም በቀጣይ ውይይት እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠዋት ቀጠሮ ተይዞ የዕለቱ ውይይት አብቅቷል፡፡

EMF

posted by Gheremew Araghaw

Single Post Navigation

Leave a comment